2ኛ ወደ ቆሮንቶስ ሰዎች 11

<< 2ኛ ወደ ቆሮንቶስ ሰዎች 11 >>
2 Corinthians 11 Amharic NT
 

1 በጥቂቱ ሞኝነቴ ብትታገሡኝ መልካም ይሆን ነበር፤ ቢሆንም በእርግጥ ታገሡኝ። 2 በእግዚአብሔር ቅንዓት እቀናላችኋለሁና፥ እንደ ንጽሕት ድንግል እናንተን ለክርስቶስ ላቀርብ ለአንድ ወንድ አጭቻችኋለሁና፤ 3 ነገር ግን እባብ በተንኮሉ ሔዋንን እንዳሳታት፥ አሳባችሁ ተበላሽቶ ለክርስቶስ ከሚሆን ቅንነትና ንጽሕና ምናልባት እንዳይለወጥ ብዬ እፈራለሁ። 4 የሚመጣውም ያልሰበክነውን ሌላ ኢየሱስ ቢሰብክ፥ ወይም ያላገኛችሁትን ልዩ መንፈስ ወይም ያልተቀበላችሁትን ልዩ ወንጌል ብታገኙ፥ በመልካም ትታገሡታላችሁ። 5 ከእነዚህ ከዋነኞቹ ሐዋርያት በአንድ ነገር እንኳ እንደ ጎደልሁ ራሴን አልቆጥርም። 6 በአነጋገሬ ያልተማርሁ ብሆን እንኳ፥ በእውቀት ግን እንዲህ አይደለሁም። ነገር ግን በሰው ሁሉ መካከል በነገር ሁሉ ተገልጠንላችኋል።

7 ወይስ የእግዚአብሔርን ወንጌል ያለ ደመወዝ ስለ ሰበክሁላችሁ፥ እናንተ ከፍ እንድትሉ ራሴን እያዋረድሁ ኃጢአት አድርጌ ይሆንን? 8 እናንተን ለማገልገል ደመወዝ እየተቀበልሁ ሌሎችን አብያተ ክርስቲያናት ዘረፍሁ። 9 ከእናንተም ጋር ሳለሁ በጎደለኝ ጊዜ፥ በማንም አልከበድሁበትም፤ ከመቄዶንያ የመጡት ወንድሞች የጎደለኝን በሙሉ ሰጥተዋልና፤ በነገርም ሁሉ እንዳልከብድባችሁ ተጠነቀቅሁ እጠነቀቅማለሁ። 10 የክርስቶስ እውነት በእኔ እንዳለ፥ ይህ ትምክህት በእኔ ዘንድ በአካይያ አገር አይከለከልም። 11 ስለ ምን? ስለማልወዳችሁ ነውን? እግዚአብሔር ያውቃል።

12 ነገር ግን በዚያ በሚመኩበት እንደ እኛ ሆነው ሊገኙ፥ ምክንያትን ከሚፈልጉቱ ምክንያትን እቆርጥ ዘንድ አሁን የማደርገውን ከዚህ ወዲህ ደግሞ አደርጋለሁ። 13 እንደ እነዚህ ያሉ ሰዎች የክርስቶስን ሐዋርያት እንዲመስሉ ራሳቸውን እየለወጡ፥ ውሸተኞች ሐዋርያትና ተንኮለኞች ሠራተኞች ናቸውና። 14 ይህም ድንቅ አይደለም፤ ሰይጣን ራሱ የብርሃንን መልአክ እንዲመስል ራሱን ይለውጣልና። 15 እንግዲህ አገልጋዮቹ ደግሞ የጽድቅን አገልጋዮች እንዲመስሉ ራሳቸውን ቢለውጡ ታላቅ ነገር አይደለም፤ ፍጻሜአቸውም እንደ ሥራቸው ይሆናል።

16 እንደ ገና እላለሁ። ለማንም ሰው ሞኝ የሆንሁ አይምሰለው፤ ያለዚያ ግን እኔ ደግሞ ጥቂት እመካ ዘንድ እንደ ሞኝ እንኳ ሆኜ ተቀበሉኝ። 17 እንደዚህ ታምኜ ስመካ የምናገረው፥ በሞኝነት እንጂ ጌታ እንዳዘዘኝ አልናገርም። 18 ብዙዎች በዓለማዊ ነገር ስለሚመኩ እኔ ደግሞ እመካለሁ። 19 ልባሞች ስለምትሆኑ በደስታ ሞኞችን ትታገሣላችሁና፤ 20 ማንም ባሪያዎች ቢያደርጋችሁ፥ ማንም ቢበላችሁ፥ ማንም ቢቀማችሁ፥ ማንም ቢኮራባችሁ፥ ማንም ፊታችሁን በጥፊ ቢመታችሁ ትታገሣላችሁና። 21 ደካሞች መስለን እንደ ነበርን በውርደት እላለሁ። ነገር ግን በሞኝነት እላለሁ፤ ማንም በሚደፍርበት እኔ ደግሞ እደፍርበታለሁ። 22 ዕብራውያን ናቸውን? እኔ ደግሞ ነኝ። የእስራኤል ወገን ናቸውን? እኔ ደግሞ ነኝ። የአብርሃም ዘር ናቸውን? እኔ ደግሞ ነኝ። የክርስቶስ አገልጋዮች ናቸውን? 23 እንደ እብድ ሰው እላለሁ፤ እኔ እበልጣለሁ፤ በድካም አብዝቼ፥ በመገረፍ አብዝቼ፥ በመታሰር አትርፌ፥ በመሞት ብዙ ጊዜ ሆንሁ። 24 አይሁድ አንድ ሲጎድል አርባ ግርፋት አምስት ጊዜ ገረፉኝ። 25 ሦስት ጊዜ በበትር ተመታሁ፤ አንድ ጊዜ በድንጋይ ተወገርሁ፤ መርከቤ ሦስት ጊዜ ተሰበረ፤ ሌሊትና ቀን በባሕር ውስጥ ኖርሁ። 26 ብዙ ጊዜ በመንገድ ሄድሁ፤ በወንዝ ፍርሃት፥ በወንበዴዎች ፍርሃት፥ በወገኔ በኩል ፍርሃት፥ በአሕዛብ በኩል ፍርሃት፥ በከተማ ፍርሃት፥ በምድረ በዳ ፍርሃት፥ በባሕር ፍርሃት፥ በውሸተኞች ወንድሞች በኩል ፍርሃት ነበረብኝ፤ 27 በድካምና በጥረት ብዙ ጊዜም እንቅልፍ በማጣት፥ በራብና በጥም ብዙ ጊዜም በመጦም፥ በብርድና በራቁትነት ነበርሁ። 28 የቀረውንም ነገር ሳልቆጥር፥ ዕለት ዕለት የሚከብድብኝ የአብያተ ክርስቲያናት ሁሉ አሳብ ነው። 29 የሚደክም ማን ነው፥ እኔም አልደክምምን? የሚሰናከል ማን ነው፥ እኔም አልናደድምን?

30 ትምክህት የሚያስፈልግ ከሆነ፥ ከድካሜ በሚሆነው ነገር እመካለሁ። 31 ለዘላለም የተባረከ የጌታችን የኢየሱስ ክርስቶስ አምላክና አባት እንዳልዋሽ ያውቃል። 32 በደማስቆ አርስጦስዮስ ከተባለ ንጉሥ በታች የሆነ የሕዝብ ገዥ ሊይዘኝ እየወደደ የደማስቆ ሰዎችን ከተማ ያስጠብቅ ነበር፥ 33 በቅጥሩም ባለ መስኮት በቅርጫት አወረዱኝና ከእጁ አመለጥሁ።


<< 2 Corinthians 11 >>
Revised Amharic Bible in XML (2003). Printed version by United Bible Societies (C)1962. E-Text in transliterated ASCII format by Lapsley/Brooks Foundation 1994. Unicode UTF-8 transformation and XML-tagging by Dirk Röckmann 2003 (www.nt-text.net). -- With kind permission of the Bible Society of Ethiopia. Every non-commercial work using this data in any form must fully include this copyright statement! Every commercial use of parts or the complete data in any form needs written permission of the Bible Society of Ethiopia!

Biblos.com Online Bible