2ኛ ወደ ቆሮንቶስ ሰዎች 10

<< 2ኛ ወደ ቆሮንቶስ ሰዎች 10 >>
2 Corinthians 10 Amharic NT
 

1 እኔም ራሴ ጳውሎስ፥ በእናንተ ዘንድ ፊት ለፊት ሳለሁ ትሑት የሆንሁ፥ ከእናንተ ግን ብርቅ የምደፍራችሁ፥ በክርስቶስ የዋህነትና ገርነት እመክራችኋለሁ፤ 2 በዓለማዊ ልማድ እንደምንመላለስ በሚቆጥሩን በአንዳንዶች ላይ አምኜ ልደፍር አስባለሁ፥ በዚያ እምነት ግን ከእናንተ ጋር ሆኜ እንዳልደፍር እለምንችኋለሁ። 3 በሰው ልማድ ምንም እንኳ የምንመላለስ ብንሆን፥ እንደ ሰው ልማድ አንዋጋም፤ 4 የጦር ዕቃችን ሥጋዊ አይደለምና፥ ምሽግን ለመስበር ግን በእግዚአብሔር ፊት ብርቱ ነው፤ 5 የሰውንም አሳብ በእግዚአብሔርም እውቀት ላይ የሚነሣውን ከፍ ያለውን ነገር ሁሉ እናፈርሳለን ለክርስቶስም ለመታዘዝ አእምሮን ሁሉ እንማርካለን፥ 6 መታዘዛችሁም በተፈጸመች ጊዜ አለመታዘዝን ሁሉ ልንበቀል ተዘጋጅተናል።

7 በፊታችሁ ያለውን ተመልከቱ። ማንም የክርስቶስ መሆኑን ተረድቶ ቢሆን፥ ይህን እንደ ገና በራሱ ይቁጠረው፤ እርሱ የክርስቶስ እንደ ሆነ እኛ ደግሞ እንዲሁ ነን። 8 ጌታ እናንተን ለማነጽ እንጂ እናንተን ለማፍረስ ያይደለ በሰጠው በሥልጣናችን ከፊት ይልቅ ብመካ እንኳ አላፍርም። 9 በመልእክቶቼ የማስደነግጣችሁ አይምሰላችሁ። 10 መልእክቶቹስ ከባድና ኃይለኛ ናቸው፥ ሰውነቱ ግን ሲታይ ደካማ ነው፥ ንግግሩም የተናቀ ነው ይላሉና። 11 እንዲሁ የሚል ይህን ይቁጠረው፤ በሩቅ ሳለን በመልእክታችን በኩል በቃል እንዳለን፥ በፊቱ ደግሞ ሳለን በሥራ እንዲሁ ነን።

12 ራሳቸውን ከሚያመሰግኑ ከአንዳንዶች ጋር ራሳችንን ልንቆጥር ወይም ራሳችንን ልናስተያይ አንደፍርምና፤ ነገር ግን እነርሱ ራሳቸውን ከራሳቸው ጋር ሲያመዛዝኑ፥ ራሳቸውንም ከራሳቸው ጋር ሲያስተያዩ፥ አያስተውሉም። 13 እኛ ግን እግዚአብሔር እንደ ወሰነልን እስከ እናንተ እንኳ እንደሚደርስ እንደ ክፍላችን ልክ እንጂ ያለ ልክ አንመካም። 14 ወደ እናንተ እንደማንደርስ አድርገን ከመጠን አናልፍምና፥ የክርስቶስን ወንጌል በመስበክ እስከ እናንተ እንኳ ደርሰናልና፤ 15 በሌሎች ድካም ያለ ልክ አንመካም፥ ነገር ግን እምነታችሁ ሲያድግ ከእናንተ ወዲያ ባለው አገር እስክንሰብክ ሥራችንን እየጨመርን፥ በክፍላችን በእናንተ ዘንድ እንድንከብር ተስፋ እናደርጋለን፤ በሌላው ክፍል ስለ ተዘጋጀው ነገር አንመካም። 16  17 የሚመካ ግን በጌታ ይመካ፤ እግዚአብሔር የሚያመሰግነው እንጂ ራሱን የሚያመሰግን እርሱ ተፈትኖ የሚወጣ አይደለምና። 18 


<< 2 Corinthians 10 >>
Revised Amharic Bible in XML (2003). Printed version by United Bible Societies (C)1962. E-Text in transliterated ASCII format by Lapsley/Brooks Foundation 1994. Unicode UTF-8 transformation and XML-tagging by Dirk Röckmann 2003 (www.nt-text.net). -- With kind permission of the Bible Society of Ethiopia. Every non-commercial work using this data in any form must fully include this copyright statement! Every commercial use of parts or the complete data in any form needs written permission of the Bible Society of Ethiopia!

Biblos.com Online Bible