የዮሐንስ ራእይ 18
Amharic NT

1ከዚህ በኋላ ታላቅ ስልጣን ያለው ሌላ መልአክ ከሰማይ ሲወርድ አየሁ፥ ከክብሩም የተነሣ ምድር በራች። 2በብርቱም ድምፅ። ታላቂቱ ባቢሎን ወደቀች፥ ወደቀች፥ የአጋንንትም ማደሪያ ሆነች፥ የርኵሳንም መናፍስት ሁሉ መጠጊያ የርኵሳንና የተጠሉም ወፎች ሁሉ መጠጊያ ሆነች፤ 3አሕዛብ ሁሉ ከዝሙትዋ ቍጣ ወይን ጠጅ የተነሳ ወድቀዋልና፥ የምድርም ነገሥታት ከእርስዋ ጋር ሴሰኑ የምድርም ነጋዴዎች ከቅምጥልነትዋ ኃይል የተነሳ ባለ ጠጋዎች ሆኑ ብሎ ጮኸ።

4ከሰማይም ሌላ ድምፅ ሰማሁ እንዲህ ሲል። ሕዝቤ ሆይ፥ በኃጢአትዋ እንዳትተባበሩ ከመቅሠፍትዋም እንዳትቀበሉ ከእርስዋ ዘንድ ውጡ፤ 5ኃጢአትዋ እስከ ሰማይ ድረስ ደርሶአልና፥ እግዚአብሔርም ዓመፃዋን አሰበ። 6እርስዋ እንደ ሰጠች መጠን ብድራት መልሱላት፥ እንደ ሥራዋም ሁለት እጥፍ ደርቡባት፤ በቀላቀለችው ጽዋ ሁለት እጥፍ አድርጋችሁ ቀላቅሉባት፤ 7ራስዋን እንደ አከበረችና እንደ ተቀማጠለች ልክ ሥቃይና ኀዘን ስጡአት። በልብዋ። ንግሥት ሆኜ እቀመጣለሁ ባልቴትም አልሆንም ኀዘንም ከቶ አላይም ስላለች፥ 8ስለዚህ በአንድ ቀን ሞትና ኀዘን ራብም የሆኑ መቅሰፍቶችዋ ይመጣሉ፥ በእሳትም ትቃጠላለች፤ የሚፈርድባት እግዚአብሔር ብርቱ ነውና።

9ከእርስዋም ጋር የሴሰኑና የተቀማጠሉ የምድር ነገሥታት የመቃጠልዋን ጢስ ሲያዩ ስለ እርስዋ ዋይ ዋይ እያሉ ያለቅሳሉ፤ 10ሥቃይዋንም ከመፍራት የተነሣ በሩቅ ቆመው። አንቺ ታላቂቱ ከተማ፥ ብርቱይቱ ከተማ ባቢሎን፥ ወዮልሽ፥ ወዮልሽ፥ በአንድ ሰዓት ፍርድሽ ደርሶአልና እያሉ ይናገራሉ።

11የመርከባቸውንም ጭነት ከእንግዲህ ወዲህ የሚገዛ የለምና የምድር ነጋዴዎች ያለቅሱላታል ያዝኑላትማል፤ 12ጭነትም ወርቅና ብር የከበረም ድንጋይ ዕንቁም፥ ቀጭንም ተልባ እግር ቀይም ሐርም ሐምራዊም ልብስ የሚሸትም እንጨት ሁሉ፥ ከዝሆን ጥርስም የተሰራ ዕቃ ሁሉ፥ እጅግም ከከበረ እንጨት ከናስም ከብረትም ከዕብነ በረድም የተሰራ ዕቃ ሁሉ፥ 13ቀረፋም ቅመምም የሚቃጠልም ሽቱ ቅባትም ዕጣንም የወይን ጠጅም ዘይትም የተሰለቀ ዱቄትም ስንዴም ከብትም በግም ፈረስም ሰረገላም ባሪያዎችም የሰዎችም ነፍሳት ነው። 14ነፍስሽም የጎመጀችው ፍሬ ከአንቺ ዘንድ አልፎአል፥ የሚቀማጠልና የሚያጌጥም ነገር ሁሉ ጠፍቶብሻል፥ ሰዎችም ከእንግዲህ ወዲህ ከቶ አያገኙአቸውም። 15እነዚህን የነገዱ በእርስዋም ባለ ጠጋዎች የሆኑት እያለቀሱና እያዘኑ። በቀጭን ተልባ እግርና በቀይ ሐምራዊም ልብስ ለተጐናጸፈች በወርቅና በከበረ ድንጋይም በዕንቁም ለተሸለመች ለታላቂቱ ከተማ ወዮላት፥ ወዮላት፥ ይህን የሚያህል ታላቅ ባለ ጠግነት በአንድ ሰዓት ጠፍቶአልና እያሉ ስቃይዋን ከመፍራት የተነሣ በሩቅ ይቆማሉ። የመርከብም መሪ ሁሉ በመርከብም ወደ ማናቸውም ስፍራ የሚሄድ ሁሉ መርከበኞችም ከባሕርም የሚጠቀሙ ሁሉ በሩቅ ቆሙ፥ 16 17 18የመቃጠልዋንም ጢስ ባዩ ጊዜ። ታላቂቱን ከተማ የምትመስላት ምን ከተማ ነበረች? እያሉ ጮኹ። 19በራሳቸውም ላይ ትቢያ ነስንሰው እያለቀሱና እያዘኑ። በባሕር መርከቦች ያሉአቸውን ሁሉ ከባለ ጠግነትዋ የተነሣ ባለ ጠጋዎች ላደረገች ለታላቂቱ ከተማ ወዮላት፥ ወዮላት፥ በአንድ ሰዓት ጠፍታለችና እያሉ ጮኹ።

20ሰማይ ሆይ፥ ቅዱሳን ሐዋርያት ነቢያትም ሆይ፥ በእርስዋ ላይ ደስ ይበላችሁ፥ እግዚአብሔር ፈርዶላችኋልና።

21አንድም ብርቱ መልአክ ትልቅን ወፍጮ የሚመስልን ድንጋይ አንስቶ ወደ ባሕር ወረወረው እንዲህ ሲል። ታላቂቱ ከተማ ባቢሎን እንዲህ ተገፍታ ትወድቃለች ከእንግዲህም ወዲህ ከቶ አትገኝም። 22በገና የሚመቱና የሚዘምሩም ድምፅ እንቢልታንና መለከትንም የሚነፉ ድምፅ ከእንግዲህ ወዲህ በአንቺ ውስጥ ከቶ አይሰማም፥ የእጅ ጥበብም ሁሉ አንድ ብልሃተኛ እንኳ ከእንግዲህ ወዲህ በአንቺ ውስጥ ከቶ አይገኝም፥ የወፍጮ ድምጽም ከእንግዲህ ወዲህ በአንቺ ውስጥ ከቶ አይሰማም፥ 23የመብራትም ብርሃን ከእንግዲህ ወዲህ በአንቺ ውስጥ ከቶ አይበራም፥ የሙሽራና የሙሽራይቱም ድምጽ ከእንግዲህ ወዲህ በአንቺ ውስጥ ከቶ አይሰማም፤ ነጋዴዎችሽ የምድር መኳንንት ነበሩና፥ በአስማትሽም አሕዛብ ሁሉ ስተዋልና። 24በእርስዋም ውስጥ የነቢያትና የቅዱሳን ደም በምድርም የታረዱ ሁሉ ደም ተገኘባት።

Revised Amharic Bible in XML (2003). Printed version by United Bible Societies (C)1962. E-Text in transliterated ASCII format by Lapsley/Brooks Foundation 1994. Unicode UTF-8 transformation and XML-tagging by Dirk Röckmann 2003 (www.nt-text.net). -- With kind permission of the Bible Society of Ethiopia. Every non-commercial work using this data in any form must fully include this copyright statement! Every commercial use of parts or the complete data in any form needs written permission of the Bible Society of Ethiopia!

Bible Hub

Revelation 17
Top of Page
Top of Page