የማቴዎስ ወንጌል 27
Amharic NT

1ሲነጋም የካህናት አለቆችና የሕዝቡ ሽማግሎች ሁሉ ሊገድሉት በኢየሱስ ላይ ተማከሩ፤ 2አስረውም ወሰዱት፥ ለገዢው ለጴንጤናዊው ጲላጦስም አሳልፈው ሰጡት።

3በዚያን ጊዜ አሳልፎ የሰጠው ይሁዳ እንደ ተፈረደበት አይቶ ተጸጸተ፥ ሠላሳውንም ብር ለካህናት አለቆችና ለሽማግሎች መልሶ። 4ንጹሕ ደም አሳልፌ በመስጠቴ በድያለሁ አለ። እነርሱ ግን። እኛስ ምን አግዶን? አንተው ተጠንቀቅ አሉ። 5ብሩንም በቤተ መቅደስ ጥሎ ሄደና ታንቆ ሞተ። 6የካህናት አለቆችም ብሩን አንሥተው። የደም ዋጋ ነውና ወደ መባ ልንጨምረው አልተፈቀደም አሉ። 7ተማክረውም የሸክላ ሠሪውን መሬት ለእንግዶች መቃብር ገዙበት። 8ስለዚህ ያ መሬት እስከ ዛሬ ድረስ የደም መሬት ተባለ። 9በዚያን ጊዜ በነቢዩ በኤርምያስ የተባለው። ከእስራኤል ልጆችም አንዳንዶቹ የገመቱትን፥ የተገመተውን ዋጋ ሠላሳ ብር ያዙ፥ 10ጌታም እንዳዘዘኝ ስለ ሸክላ ሠሪ መሬት ሰጡት። የሚል ተፈጸመ።

11ኢየሱስም በገዢው ፊት ቆመ፤ ገዢውም። የአይሁድ ንጉሥ አንተ ነህን? ብሎ ጠየቀው፤ ኢየሱስም። አንተ አልህ አለው። 12የካህናት አለቆችም ሽማግሎችም ሲከሱት ምንም አልመለሰም። 13በዚያን ጊዜ ጲላጦስ። ስንት ያህል እንዲመሰክሩብህ አትሰማምን? አለው። 14ገዢውም እጅግ እስኪደነቅ ድረስ አንዲት ቃል ስንኳ አልመለሰለትም።

15በዚያም በዓል ሕዝቡ የወደዱትን አንድ እስረኛ ሊፈታላቸው ለገዢው ልማድ ነበረው። 16በዚያን ጊዜም በርባን የሚባል በጣም የታወቀ እስረኛ ነበራቸው። 17እንግዲህ እነርሱ ተሰብስበው ሳሉ ጲላጦስ። በርባንን ወይስ ክርስቶስ የተባለውን ኢየሱስን ማንኛውን ልፈታላችሁ ትወዳላችሁ? አላቸው፤ 18በቅንዓት አሳልፈው እንደ ሰጡት ያውቅ ነበርና።

19እርሱም በፍርድ ወንበር ተቀምጦ ሳለ ሚስቱ። ስለ እርሱ ዛሬ በሕልም እጅግ መከራ ተቀብያለሁና በዚያ ጻድቅ ሰው ምንም አታድርግ ብላ ላከችበት። 20የካህናት አለቆችና ሽማግሎች ግን በርባንን እንዲለምኑ ኢየሱስን ግን እንዲያጠፉ ሕዝቡን አባበሉ። 21ገዢውም መልሶ። ከሁለቱ ማንኛውን ልፈታላችሁ ትወዳላችሁ? አላቸው፤ እነርሱም። በርባንን አሉ። 22ጲላጦስ። ክርስቶስ የተባለውን ኢየሱስን እንግዲህ ምን ላድርገው? አላቸው፤ ሁሉም። ይሰቀል አሉ። 23ገዢውም። ምን ነው? ያደረገው ክፋት ምንድር ነው? አለ፤ እነርሱ ግን። ይሰቀል እያሉ ጩኸት አበዙ።

24ጲላጦስም ሁከት እንዲጀመር እንጂ አንዳች እንዳይረባ ባየ ጊዜ፥ ውኃ አንሥቶ። እኔ ከዚህ ጻድቅ ሰው ደም ንጹሕ ነኝ፤ እናንተ ተጠንቀቁ ሲል በሕዝቡ ፊት እጁን ታጠበ። 25ሕዝቡም ሁሉ መልሰው። ደሙ በእኛና በልጆቻችን ላይ ይሁን አሉ። 26በዚያን ጊዜ በርባንን ፈታላቸው፥ ኢየሱስን ግን ገርፎ ሊሰቀል አሳልፎ ሰጠ።

27በዚያን ጊዜ የገዢው ወታደሮች ኢየሱስን ወደ ገዢው ግቢ ውስጥ ወሰዱት ጭፍራውንም ሁሉ ወደ እርሱ አከማቹ። 28ልብሱንም ገፈው ቀይ ልብስ አለበሱት፥ 29ከእሾህም አክሊል ጎንጉነው በራሱ ላይ፥ በቀኝ እጁም መቃ አኖሩ፥ በፊቱም ተንበርክከው። የአይሁድ ንጉሥ ሆይ፥ ሰላም ለአንተ ይሁን እያሉ ዘበቱበት፤ 30ተፉበትም መቃውንም ይዘው ራሱን መቱት። 31ከዘበቱበትም በኋላ ቀዩን ልብስ ገፈፉት፥ ልብሱንም አለበሱት ሊሰቅሉትም ወሰዱት።

32ሲወጡም ስምዖን የተባለው የቀሬናን ሰው አገኙ፤ እርሱንም መስቀሉን ይሸከም ዘንድ አስገደዱት።

33ትርጓሜው የራስ ቅል ስፍራ ወደሚሆን ጎልጎታ ወደሚባለው ስፍራ በደረሱ ጊዜም፥ 34በሐሞት የተደባለቀ የወይን ጠጅ ሊጠጣ አቀረቡለት፤ ቀምሶም ሊጠጣው አልወደደም።

35ከሰቀሉትም በኋላ ልብሱን ዕጣ ጥለው ተካፈሉ፥ 36በዚያም ተቀምጠው ይጠብቁት ነበር። 37ይህ ኢየሱስ የአይሁድ ንጉሥ ነው የሚል የክሱን ጽሕፈት ከራሱ በላይ አኖሩ።

38በዚያን ጊዜ ሁለት ወንበዶች አንዱ በቀኝ አንዱም በግራ ከእርሱ ጋር ተሰቀሉ። 39የሚያልፉትም ራሳቸውን እየነቀነቁ ይሰድቡት ነበርና። 40ቤተ መቅደስን የምታፈርስ በሦስት ቀንም የምትሠራው፥ ራስህን አድን፤ የእግዚአብሔር ልጅስ ከሆንህ ከመስቀል ውረድ አሉት። 41እንዲሁም ደግሞ የካህናት አለቆች ከጻፎችና ከሽማግሎች ጋር እየዘበቱበት እንዲህ አሉ። 42ሌሎችን አዳነ፥ ራሱን ሊያድን አይችልም፤ የእስራኤል ንጉሥ ከሆነ፥ አሁን ከመስቀል ይውረድ እኛም እናምንበታለን። 43በእግዚአብሔር ታምኖአል፤ የእግዚአብሔር ልጅ ነኝ ብሎአልና ከወደደውስ አሁን ያድነው። 44ከእርሱ ጋር የተሰቀሉት ወንበዶች ደግሞ ያንኑ እያሉ ይነቅፉት ነበር።

45ከስድስት ሰዓትም ጀምሮ እስከ ዘጠኝ ሰዓት ድረስ በምድር ሁሉ ላይ ጨለማ ሆነ። 46በዘጠኝ ሰዓትም ኢየሱስ። ኤሎሄ ኤሎሄ ላማ ሰበቅታኒ? ብሎ በታላቅ ድምፅ ጮኸ። ይህም። አምላኬ አምላኬ፥ ስለ ምን ተውኸኝ? ማለት ነው። 47በዚያም ከቆሙት ሰዎች ሰምተው። ይህስ ኤልያስን ይጠራል አሉ። 48ወዲያውም ከእነርሱ አንዱ ሮጠ፤ ሰፍነግም ይዞ ሆምጣጤ ሞላበት፥ በመቃም አድርጎ አጠጣው። 49ሌሎቹ ግን። ተው፥ ኤልያስ መጥቶ ያድነው እንደ ሆነ እንይ አሉ። 50ኢየሱስም ሁለተኛ በታላቅ ድምፅ ጮኾ ነፍሱን ተወ። 51እነሆም፥ የቤተ መቅደስ መጋረጃ ከላይ እስከ ታች ከሁለት ተቀደደ፥ ምድርም ተናወጠች፥ ዓለቶችም ተሰነጠቁ፤ 52መቃብሮችም ተከፈቱ፥ ተኝተው ከነበሩትም ከቅዱሳን ብዙ ሥጋዎች ተነሡ፤ 53ከትንሣኤውም በኋላ ከመቃብሮች ወጥተው ወደ ቅድስት ከተማ ገቡና ለብዙዎች ታዩ። 54የመቶ አለቃም ከእርሱም ጋር ኢየሱስን የሚጠብቁ መናወጡንና የሆነውን ነገር አይተው። ይህ በእውነት የእግዚአብሔር ልጅ ነበረ ብለው እጅግ ፈሩ።

55ኢየሱስን እያገለገሉ ከገሊላ የተከተሉት ብዙ ሴቶች በሩቅ ሆነው ሲመለከቱ በዚያ ነበሩ፤ 56ከእነርሱም መግደላዊት ማርያምና የያዕቆብና የዮሳ እናት ማርያም የዘብዴዎስም የልጆቹ እናት ነበሩ።

57በመሸም ጊዜ ዮሴፍ የተባለው ባለ ጠጋ ሰው ከአርማትያስ መጣ፥ እርሱም ደግሞ የኢየሱስ ደቀ መዝሙር ነበረ፤ 58ይኸውም ወደ ጲላጦስ ቀርቦ የኢየሱስን ሥጋ ለመነው። 59ጲላጦስም እንዲሰጡት አዘዘ። ዮሴፍም ሥጋውን ይዞ በንጹሕ በፍታ ከፈነው፥ 60ከዓለት በወቀረው በአዲሱ መቃብርም አኖረው፥ በመቃብሩም ደጃፍ ታላቅ ድንጋይ አንከባሎ ሄደ። 61መግደላዊት ማርያምም ሁለተኛይቱም ማርያም በመቃብሩ አንጻር ተቀምጠው በዚያ ነበሩ።

62በማግሥቱም ከመዘጋጀት በኋላ በሚሆነው ቀን፥ የካህናት አለቆችና ፈሪሳውያን ወደ ጲላጦስ ተሰበሰቡና። 63ጌታ ሆይ፥ ያ አሳች በሕይወቱ ገና ሳለ። ከሦስት ቀን በኋላ እነሣለሁ እንዳለ ትዝ አለን። 64እንግዲህ ደቀ መዛሙርቱ መጥተው በሌሊት እንዳይሰርቁት ለሕዝቡም። ከሙታን ተነሣ እንዳይሉ፥ የኋለኛይቱ ስሕተት ከፊተኛይቱ ይልቅ የከፋች ትሆናለችና መቃብሩ እስከ ሦስተኛ ቀን ድረስ እንዲጠበቅ እዘዝ አሉት። 65ጲላጦስም። ጠባቆች አሉአችሁ፤ ሄዳችሁ እንዳወቃችሁ አስጠብቁ አላቸው። 66እነርሱም ሄደው ከጠባቆች ጋር ድንጋዩን አትመው መቃብሩን አስጠበቁ።

Revised Amharic Bible in XML (2003). Printed version by United Bible Societies (C)1962. E-Text in transliterated ASCII format by Lapsley/Brooks Foundation 1994. Unicode UTF-8 transformation and XML-tagging by Dirk Röckmann 2003 (www.nt-text.net). -- With kind permission of the Bible Society of Ethiopia. Every non-commercial work using this data in any form must fully include this copyright statement! Every commercial use of parts or the complete data in any form needs written permission of the Bible Society of Ethiopia!

Bible Hub

Matthew 26
Top of Page
Top of Page