የማቴዎስ ወንጌል 22
Amharic NT

1ኢየሱስም መለሰ ደግሞም በምሳሌ ነገራቸው እንዲህም አለ። 2መንግሥተ ሰማያት ለልጁ ሰርግ ያደረገ ንጉሥን ትመስላለች። 3የታደሙትንም ወደ ሰርጉ ይጠሩ ዘንድ ባሮቹን ላከ ሊመጡም አልወደዱም። 4ደግሞ ሌሎችን ባሮች ልኮ። የታደሙትን። እነሆ፥ ድግሴን አዘጋጀሁ፥ ኮርማዎቼና የሰቡት ከብቶቼ ታርደዋል፥ ሁሉም ተዘጋጅቶአል፤ ወደ ሰርጉ ኑ በሉአቸው አለ። 5እነርሱ ግን ቸል ብለው አንዱ ወደ እርሻው፥ ሌላውም ወደ ንግዱ ሄደ፤ 6የቀሩትም ባሮቹን ይዘው አንገላቱአቸው ገደሉአቸውም። 7ንጉሡም ተቈጣ፥ ጭፍሮቹንም ልኮ እነዚያን ገዳዮች አጠፋ፤ ከተማቸውንም አቃጠለ። 8በዚያን ጊዜ ባሮቹን። ሰርጉስ ተዘጋጅቶአል፥ ነገር ግን የታደሙት የማይገባቸው ሆኑ፤ 9እንግዲህ ወደ መንገድ መተላለፊያ ሄዳችሁ ያገኛችሁትን ሁሉ ወደ ሰርጉ ጥሩ አለ። 10እነዚያም ባሮች ወደ መንገድ ወጥተው ያገኙትን ሁሉ ክፉዎችንም በጎዎችንም ሰበሰቡ፤ የሰርጉንም ቤት ተቀማጮች ሞሉት።

11ንጉሡም የተቀመጡትን ለማየት በገባ ጊዜ በዚያ የሰርግ ልብስ ያለበሰ አንድ ሰው አየና። ወዳጄ ሆይ፥ 12የሰርግ ልብስ ሳትለብስ እንዴት ወደዚህ ገባህ? አለው እርሱም ዝም አለ። 13በዚያን ጊዜ ንጉሡ አገልጋዮቹን። እጁንና እግሩን አስራችሁ በውጭ ወዳለው ጨለማ አውጡት፤ በዚያ ልቅሶና ጥርስ ማፋጨት ይሆናል አለ። 14የተጠሩ ብዙዎች፥ የተመረጡ ግን ጥቂቶች ናቸውና።

15ስለዚህ ፈሪሳውያን ሄዱና እንዴት አድርገው በነገር እንዲያጠምዱት ተማከሩ። 16ደቀ መዛሙርታቸውንም ከሄሮድስ ወገን ጋር ላኩበት፥ እነርሱም። መምህር ሆይ፥ እውነተኛ እንደ ሆንህ በእውነትም የእግዚአብሔርን መንገድ እንድታስተምር እናውቃለን፥ ለማንምም አታደላም፥ የሰውን ፊት አትመለከትምና፤ 17እንግዲህ ምን ይመስልሃል? ንገረን ለቄሣር ግብር መስጠት ተፈቅዶአልን ወይስ አልተፈቀደም? አሉት። 18ኢየሱስም ክፋታቸውን አውቆ። እናንተ ግብዞች፥ ስለ ምን ትፈትኑኛላችሁ? 19የግብሩን ብር አሳዩኝ አለ። እነርሱም ዲናር አመጡለት። 20እርሱም። ይህች መልክ ጽሕፈቲቱስ የማን ናት? አላቸው። 21የቄሣር ነው አሉት። በዚያን ጊዜ። እንኪያስ የቄሣርን ለቄሣር የእግዚአብሔርንም ለእግዚአብሔር አስረክቡ አላቸው። 22ይህንም ሰምተው ተደነቁ፥ ትተውትም ሄዱ።

23በዚያን ቀን። ትንሣኤ ሙታን የለም የሚሉ ሰዱቃውያን ወደ እርሱ ቀረቡ፥ 24እንዲህም ብለው ጠየቁት። መምህር ሆይ፥ ሙሴ አንድ ሰው ልጅ ሳይወልድ ሲሞት ወንድሙ ሚስቱን አግብቶ ለወንድሙ ዘር ይተካ አለ። 25ሰባት ወንድማማች በእኛ ዘንድ ነበሩ፤ ፊተኛውም ሚስት አግብቶ ሞተ፥ ዘርም ስለሌለው ሚስቱን ለወንድሙ ተወለት፤ 26እንዲሁ ደግሞ ሁለተኛው ሦስተኛውም፥ እስከ ሰባተኛው ድረስ። 27ከሁሉም በኋላ ሴቲቱ ሞተች። 28ሁሉ አግብተዋታልና በትንሣኤ ቀንስ፥ ከሰባቱ ለማናቸው ሚስት ትሆናለች?

29ኢየሱስም መልሶ እንዲህ አላቸው። መጻሕፍትንና የእግዚአብሔርን ኃይል አታውቁምና ትስታላችሁ። 30በትንሣኤስ እንደ እግዚአብሔር መላእክት በሰማይ ይሆናሉ እንጂ አያገቡም አይጋቡምም። 31ስለ ትንሣኤ ሙታን ግን። እኔ የአብርሃም አምላክ፥ የይስሐቅም አምላክ የያዕቆብም አምላክ ነኝ የሚል ከእግዚአብሔር ዘንድ ወደ እናንተ የተባለውን አላነበባችሁምን? የሕያዋን አምላክ ነው እንጂ የሙታን አይደለም። 32 33ሕዝቡም ይህን ሰምተው በትምህርቱ ተገረሙ።

34ፈሪሳውያንም ሰዱቃውያንን ዝም እንዳሰኛቸው በሰሙ ጊዜ አብረው ተሰበሰቡ። 35ከእነርሱም አንድ ሕግ አዋቂ ሊፈትነው። 36መምህር ሆይ፥ ከሕግ ማናቸይቱ ትእዛዝ ታላቅ ናት? ብሎ ጠየቀው። 37ኢየሱስም እንዲህ አለው። ጌታ አምላክህን በፍጹም ልብህ በፍጹም ነፍስህም በፍጹም አሳብህም ውደድ። 38ታላቂቱና ፊተኛይቱ ትእዛዝ ይህች ናት። 39ሁለተኛይቱም ይህችን ትመስላለች፥ እርስዋም። ባልንጀራህን እንደ ነፍስህ ውደድ የምትለው ናት። 40በእነዚህ በሁለቱ ትእዛዛት ሕጉም ሁሉ ነቢያትም ተሰቅለዋል።

41ፈሪሳውያንም ተሰብስበው ሳሉ፥ ኢየሱስ። ስለ ክርስቶስ ምን ይመስላችኋል? የማንስ ልጅ ነው? ብሎ ጠየቃቸው። የዳዊት ልጅ ነው አሉት። 42 43እርሱም። እንኪያስ ዳዊት። ጌታ ጌታዬን። ጠላቶችህን የእግርህ መረገጫ እስካደርግልህ ድረስ በቀኜ ተቀመጥ አለው ሲል እንዴት በመንፈስ ጌታ ብሎ ይጠራዋል?

44

45ዳዊትስ ጌታ ብሎ ከጠራው፥ እንዴት ልጁ ይሆናል? አላቸው። 46አንድም ቃል ስንኳ ይመልስለት ዘንድ የተቻለው የለም፥ ከዚያ ቀንም ጀምሮ ወደ ፊት ማንም ሊጠይቀው አልደፈረም።

Revised Amharic Bible in XML (2003). Printed version by United Bible Societies (C)1962. E-Text in transliterated ASCII format by Lapsley/Brooks Foundation 1994. Unicode UTF-8 transformation and XML-tagging by Dirk Röckmann 2003 (www.nt-text.net). -- With kind permission of the Bible Society of Ethiopia. Every non-commercial work using this data in any form must fully include this copyright statement! Every commercial use of parts or the complete data in any form needs written permission of the Bible Society of Ethiopia!

Bible Hub

Matthew 21
Top of Page
Top of Page