የማቴዎስ ወንጌል 21
Amharic NT

1ወደ ኢየሩሳሌምም ቀርበው ወደ ደብረ ዘይት ወደ ቤተ ፋጌ ሲደርሱ፥ ያንጊዜ ኢየሱስ ከደቀ መዛሙርቱ ሁለት ላከ፥ 2እንዲህም አላቸው። በፊታችሁ ወዳለችው መንደር ሂዱ፥ በዚያን ጊዜም የታሰረችን አህያ ውርንጫም ከእርስዋ ጋር ታገኛላችሁ፤ ፈትታችሁ አምጡልኝ። 3ማንም አንዳች ቢላችሁ። ለጌታ ያስፈልጉታል በሉ፤ ወዲያውም ይሰዳቸዋል። 4ለጽዮን ልጅ። እነሆ፥ ንጉሥሽ የዋህ ሆኖ በአህያ ላይና በአህያይቱ ግልገል በውርንጫይቱ ላይ ተቀምጦ ወደ አንቺ ይመጣል በሉአት ተብሎ በነቢይ የተነገረው ይፈጸም ዘንድ ይህ ሆነ።

5

6ደቀ መዛሙርቱም ሄደው ኢየሱስ እንዳዘዛቸው አደረጉ፥ 7አህያይቱንና ውርንጫዋንም አመጡለት፥ ልብሳቸውንም በእነርሱ ላይ ጫኑ፥ ተቀመጠባቸውም። 8ከሕዝቡም እጅግ ብዙዎች ልብሳቸውን በመንገድ ላይ አነጠፉ፥ ሌሎችም ከዛፍ ጫፍ ጫፉን እየቈረጡ በመንገድ ላይ ያነጥፉ ነበር።

9የሚቀድሙትም ሕዝብ የሚከተሉትም። ሆሣዕና ለዳዊት ልጅ በጌታ ስም የሚመጣ የተባረከ ነው፤ ሆሣዕና በአርያም እያሉ ይጮኹ ነበር።

10ወደ ኢየሩሳሌምም በገባ ጊዜ መላው ከተማ። ይህ ማን ነው? ብሎ ተናወጠ። 11ሕዝቡም። ይህ ከገሊላ ናዝሬት የመጣ ነቢዩ ኢየሱስ ነው አሉ።

12ኢየሱስም ወደ መቅደስ ገባና በመቅደስ የሚሸጡትንና የሚገዙትን ሁሉ አወጣ፥ የገንዘብ ለዋጮችንም ገበታዎች የርግብ ሻጮችንም ወንበሮች ገለበጠና። 13ቤቴ የጸሎት ቤት ትባላለች ተብሎ ተጽፎአል፥ እናንተ ግን የወንበዶች ዋሻ አደረጋችኋት አላቸው።

14በመቅደስም ዕውሮችና አንካሶች ወደ እርሱ ቀረቡና ፈወሳቸው። 15ነገር ግን የካህናት አለቆችና ጻፎች ያደረገውን ድንቃ ድንቅ በመቅደስም። ሆሣዕና ለዳዊት ልጅ እያሉ የሚጮኹትን ልጆች ባዩ ጊዜ፥ ተቈጥተው። 16እነዚህ የሚሉትን አትሰማምን? አሉት። ኢየሱስም። እሰማለሁ፤ ከሕፃናትና ከሚጠቡት አፍ ምስጋናን ለራስህ አዘጋጀህ የሚለውን ቃል ከቶ አላነበባችሁምን? አላቸው። 17ትቶአቸውም ከከተማ ወደ ቢታንያ ወጣ በዚያም አደረ።

18በማለዳም ወደ ከተማ ሲመለስ ተራበ። 19በመንገድም አጠገብ በለስ አይቶ ወደ እርስዋ መጣ፤ ከቅጠልም ብቻ በቀር ምንም አላገኘባትምና። ለዘላለሙ ፍሬ አይገኝብሽ አላት። በለሲቱም ያንጊዜውን ደረቀች።

20ደቀ መዛሙርቱም ይህን አይተው። በለሲቱ ያንጊዜውን እንዴት ደረቀች? ብለው ተደነቁ። 21ኢየሱስም መልሶ። እውነት እላችኋለሁ፥ እምነት ቢኖራችሁ ባትጠራጠሩም፥ በበለሲቱ እንደ ሆነባት ብቻ አታደርጉም፤ ነገር ግን ይህን ተራራ እንኳ። ተነቅለህ ወደ ባሕር ተወርወር ብትሉት ይሆናል፤ 22አምናችሁም በጸሎት የምትለምኑትን ሁሉ ትቀበላላችሁ አላቸው።

23ወደ መቅደስም ገብቶ ሲያስተምር የካህናት አለቆችና የሕዝብ ሽማግሎች ወደ እርሱ ቀረቡና። በምን ሥልጣን እነዚህን ታደርጋለህ? ይህንስ ሥልጣን ማን ሰጠህ? አሉት። 24ኢየሱስም መልሶ። እኔ ደግሞ አንዲት ነገር እጠይቃችኋለሁ፤ እናንተም ያችን ብትነግሩኝ እኔ ደግሞ እነዚህን በምን ሥልጣን እንዳደርግ እነግራችኋለሁ፤ 25የዮሐንስ ጥምቀት ከወዴት ነበረች? ከሰማይን ወይስ ከሰው? አላቸው። እነርሱም እርስ በርሳቸው ሲነጋገሩ። ከሰማይ ብንል። እንኪያስ ስለ ምን አላመናችሁበትም? ይለናል፤ 26ከሰው ግን ብንል፥ ዮሐንስን ሁሉም እንደ ነቢይ ያዩታልና ሕዝቡን እንፈራለን አሉ። 27ለኢየሱስም መልሰው። አናውቅም አሉት። እርሱም ደግሞ። እኔም በምን ሥልጣን እነዚህን እንዳደርግ አልነግራችሁም አላቸው።

28ነገር ግን ምን ይመስላችኋል? አንድ ሰው ሁለት ልጆች ነበሩት፤ ወደ አንደኛው ቀርቦ። ልጄ ሆይ፥ ዛሬ ሂድና በወይኔ አትክልት ሥራ አለው። 29እርሱም መልሶ። አልወድም አለ፤ ኋላ ግን ተጸጸተና ሄደ። 30ወደ ሁለተኛውም ቀርቦ እንዲሁ አለው እርሱም መልሶ። እሺ ጌታዬ አለ፤ ነገር ግን አልሄደም። 31ከሁለቱ የአባቱን ፈቃድ ያደረገ ማን ነው? ፊተኛው አሉት። ኢየሱስ እንዲህ አላቸው። እውነት እላችኋለሁ፥ ቀራጮችና ጋለሞቶች ወደ እግዚአብሔር መንግሥት በመግባት ይቀድሙአችኋል። 32ዮሐንስ በጽድቅ መንገድ መጥቶላችሁ ነበርና፥ አላመናችሁበትም፤ ቀራጮችና ጋለሞቶች ግን አመኑበት፤ እናንተም ይህን አይታችሁ ታምኑበት ዘንድ በኋላ ንስሐ አልገባችሁም።

33ሌላ ምሳሌ ስሙ። የወይን አትክልት የተከለ ባለቤት ሰው ነበረ፤ ቅጥርም ቀጠረለት፥ መጥመቂያም ማሰለት፥ ግንብም ሠራና ለገበሬዎች አከራይቶ ወደ ሌላ አገር ሄደ። 34የሚያፈራበትም ጊዜ ሲቀርብ፥ ፍሬውን ሊቀበሉ ባሮቹን ወደ ገበሬዎች ላከ። 35ገበሬዎቹም ባሮቹን ይዘው አንዱን ደበደቡት አንዱንም ገደሉት ሌላውንም ወገሩት። 36ደግሞ ከፊተኞች የሚበዙ ሌሎች ባሮችን ላከ፥ እንዲሁም አደረጉባቸው። 37በኋላ ግን። ልጄንስ ያፍሩታል ብሎ ልጁን ላከባቸው። 38ገበሬዎቹ ግን ልጁን ባዩ ጊዜ እርስ በርሳቸው። ወራሹ ይህ ነው፤ ኑ፥ እንግደለውና ርስቱን እናግኝ ተባባሉ። 39ይዘውም ከወይኑ አትክልት አወጡና ገደሉት። 40እንግዲህ የወይኑ አትክልት ጌታ በሚመጣ ጊዜ በእነዚህ ገበሬዎች ምን ያደርግባቸዋል? 41እነርሱም። ክፉዎችን በክፉ ያጠፋቸዋል፥ የወይኑንም አትክልት ፍሬውን በየጊዜው ለሚያስረክቡ ለሌሎች ገበሬዎች ይሰጠዋል አሉት።

42ኢየሱስ እንዲህ አላቸው። ግንበኞች የናቁት ድንጋይ እርሱ የማዕዘን ራስ ሆነ፤ ይህም ከጌታ ዘንድ ሆነ፥ ለዓይኖቻችንም ድንቅ ነው የሚለውን ከቶ በመጽሐፍ አላነበባችሁምን?

43ስለዚህ እላችኋለሁ፥ የእግዚአብሔር መንግሥት ከእናንተ ትወሰዳለች ፍሬዋንም ለሚያደርግ ሕዝብ ትሰጣለች። 44በዚህም ድንጋይ ላይ የሚወድቅ ይቀጠቀጣል፤ ድንጋዩ ግን የሚወድቅበትን ሁሉ ይፈጨዋል።

45የካህናት አለቆችና ፈሪሳውያንም ምሳሌዎቹን ሰምተው ስለ እነርሱ እንደ ተናገረ አስተዋሉ፤ 46ሊይዙትም ሲፈልጉት ሳሉ ሕዝቡ እንደ ነቢይ ስላዩት ፈሩአቸው።

Revised Amharic Bible in XML (2003). Printed version by United Bible Societies (C)1962. E-Text in transliterated ASCII format by Lapsley/Brooks Foundation 1994. Unicode UTF-8 transformation and XML-tagging by Dirk Röckmann 2003 (www.nt-text.net). -- With kind permission of the Bible Society of Ethiopia. Every non-commercial work using this data in any form must fully include this copyright statement! Every commercial use of parts or the complete data in any form needs written permission of the Bible Society of Ethiopia!

Bible Hub

Matthew 20
Top of Page
Top of Page