የማቴዎስ ወንጌል 18
Amharic NT

1በዚያች ሰዓት ደቀ መዛሙርቱ ወደ ኢየሱስ ቀርበው። በመንግሥተ ሰማያት ከሁሉ የሚበልጥ ማን ይሆን? አሉት። 2ሕፃንም ጠርቶ በመካከላቸው አቆመ 3እንዲህም አለ። እውነት እላችኋለሁ፥ ካልተመለሳችሁ እንደ ሕፃናትም ካልሆናችሁ፥ ወደ መንግሥተ ሰማያት ከቶ አትገቡም። 4እንግዲህ እንደዚህ ሕፃን ራሱን የሚያዋርድ ሁሉ፥ በመንግሥተ ሰማያት የሚበልጥ እርሱ ነው። 5እንደዚህም ያለውን አንድ ሕፃን በስሜ የሚቀበል ሁሉ እኔን ይቀበላል፤ 6በእኔም ከሚያምኑ ከነዚህ ከታናናሾቹ አንዱን የሚያሰናክል ሁሉ፥ የወፍጮ ድንጋይ በአንገቱ ታስሮ ወደ ጥልቅ ባሕር መስጠም ይሻለው ነበር።

7ወዮ ለዓለም ስለ ማሰናከያ፤ ማሰናከያ ሳይመጣ አይቀርምና፥ ነገር ግን በእርሱ ጠንቅ ማሰናከያ ለሚመጣበት ለዚያ ሰው ወዮለት።

8እጅህ ወይም እግርህ ብታሰናክልህ፥ ቈርጠህ ከአንተ ጣላት፤ ሁለት እጅ ወይም ሁለት እግር ኖሮህ ወደ ዘላለም እሳት ከምትጣል ይልቅ አንካሳ ወይም ጉንድሽ ሆነህ ወደ ህይወት መግባት ይሻልሀል። 9ዓይንህ ብታሰናክልህ አውጥተህ ከአንተ ጣላት፤ ሁለት ዓይን ኖሮህ ወደ ገሃነመ እሳት ከምትጣል ይልቅ አንዲት ዓይን ኖራህ ወደ ሕይወት መግባት ይሻልሃል።

10ከነዚህ ከታናናሾቹ አንዱን እንዳትንቁ ተጠንቀቁ፤ መላእክቶቻቸው በሰማያት ዘወትር በሰማያት ያለውን የአባቴን ፊት ያያሉ እላችኋለሁና። የሰው ልጅ የጠፋውን ለማዳን መጥቶአልና።

12ምን ይመስላችኋል? ለአንድ ሰው መቶ በጎች ቢኖሩት ከእነርሱም አንዱ ቢባዝን፥ ዘጠና ዘጠኙን በተራራ ትቶ ሄዶም የባዘነውን አይፈልግምን? 13ቢያገኘውም፥ እውነት እላችኋለሁ፥ ካልባዘኑቱ ከዘጠና ዘጠኙ ይልቅ በእርሱ ደስ ይለዋል። 14እንደዚሁ ከእነዚህ ከታናናሾቹ አንዱ እንዲጠፋ በሰማያት ያለው አባታችሁ ፈቃድ አይደለም።

15ወንድምህም ቢበድልህ፥ ሄደህ አንተና እርሱ ብቻችሁን ሆናችሁ ውቀሰው። ቢሰማህ፥ ወንድምህን ገንዘብ አደረግኸው፤ 16ባይሰማህ ግን፥ በሁለት ወይም በሦስት ምስክር አፍ ነገር ሁሉ እንዲጸና፥ ዳግመኛ አንድ ወይም ሁለት ከአንተ ጋር ውሰድ፤ 17እነርሱንም ባይሰማ፥ ለቤተ ክርስቲያን ንገራት፤ ደግሞም ቤተ ክርስቲያንን ባይሰማት፥ እንደ አረመኔና እንደ ቀራጭ ይሁንልህ። 18እውነት እላችኋለሁ፥ በምድር የምታስሩት ሁሉ በሰማይ የታሰረ ይሆናል፥ በምድርም የምትፈቱት ሁሉ በሰማይ የተፈታ ይሆናል።

19ደግሞ እላችኋለሁ፥ ከእናንተ ሁለቱ በምድር በማናቸውም በሚለምኑት ነገር ሁሉ ቢስማሙ በሰማያት ካለው ከአባቴ ዘንድ ይደረግላቸዋል። 20ሁለት ወይም ሦስት በስሜ በሚሰበሰቡበት በዚያ በመካከላቸው እሆናለሁና።

21በዚያን ጊዜ ጴጥሮስ ወደ እርሱ ቀርቦ። ጌታ ሆይ፥ ወንድሜ ቢበድለኝ ስንት ጊዜ ልተውለት? እስከ ሰባት ጊዜን? አለው። 22ኢየሱስ እንዲህ አለው። እስከ ሰባ ጊዜ ሰባት እንጂ እስከ ሰባት ጊዜ አልልህም።

23ስለዚህ መንግሥተ ሰማያት ባሮቹን ሊቈጣጠር የወደደን ንጉሥ ትመስላለች። 24መቈጣጠርም በጀመረ ጊዜ፥ እልፍ መክሊት ዕዳ ያለበትን አንድ ሰው ወደ እርሱ አመጡ። 25የሚከፍለውም ቢያጣ፥ እርሱና ሚስቱ ልጆቹም ያለውም ሁሉ እንዲሸጥና ዕዳው እንዲከፈል ጌታው አዘዘ። 26ስለዚህ ባሪያው ወድቆ ሰገደለትና። ጌታ ሆይ፥ ታገሠኝ፥ ሁሉንም እከፍልሃለሁ አለው። 27የዚያም ባሪያ ጌታ አዘነለትና ለቀቀው፥ ዕዳውንም ተወለት። 28ነገር ግን ያ ባሪያ ወጥቶ ከባልንጀሮቹ ከባሮቹ መቶ ዲናር ዕዳ ያለበትን አንዱን አገኘና። ዕዳህን ክፈለኝ ብሎ ያዘና አነቀው። 29ስለዚህ ባልንጀራው ባሪያ ወድቆ። ታገሠኝ፥ ሁሉንም እከፍልሃለሁ ብሎ ለመነው። 30እርሱም አልወደደም፥ ግን ሄዶ ዕዳውን እስኪከፍል ድረስ በወኅኒ አኖረው። 31ባልንጀሮቹ የሆኑ ባሮችም ያደረገውን አይተው እጅግ አዘኑ፥ መጥተውም የሆነውን ሁሉ ለጌታቸው ገለጡ። 32ከዚያ ወዲያ ጌታው ጠርቶ። አንተ ክፉ ባሪያ፥ ስለ ለመንኸኝ ያን ዕዳ ሁሉ ተውሁልህ፤ 33እኔ እንደ ማርሁህ ባልንጀራህ የሆነውን ያን ባሪያ ልትምረው ለአንተስ አይገባህምን? አለው። 34ጌታውም ተቈጣና ዕዳውን ሁሉ እስኪከፍለው ድረስ ለሚሣቅዩት አሳልፎ ሰጠው። 35ከእናንተ እያንዳንዱ ወንድሙን ከልቡ ይቅር ካላለ፥ እንዲሁ ደግሞ የሰማዩ አባቴ ያደርግባችኋል።

Revised Amharic Bible in XML (2003). Printed version by United Bible Societies (C)1962. E-Text in transliterated ASCII format by Lapsley/Brooks Foundation 1994. Unicode UTF-8 transformation and XML-tagging by Dirk Röckmann 2003 (www.nt-text.net). -- With kind permission of the Bible Society of Ethiopia. Every non-commercial work using this data in any form must fully include this copyright statement! Every commercial use of parts or the complete data in any form needs written permission of the Bible Society of Ethiopia!

Bible Hub

Matthew 17
Top of Page
Top of Page