የማርቆስ ወንጌል 14
Amharic NT

1ከሁለት ቀን በኋላ ፋሲካና የቂጣ በዓል ነበረ። የካህናት አለቆችም ጻፎችም እንዴት አድርገው በተንኰል እንደሚይዙትና እንደሚገድሉት ይፈልጉ ነበር። 2የሕዝብ ሁከት እንዳይሆን በበዓል አይሁን ይሉ ነበርና።

3እርሱም በቢታንያ በለምጻሙ በስምዖን ቤት በነበረ ጊዜ፥ በማዕድ ተቀምጦ ሳለ፥ አንዲት ሴት ዋጋው እጅግ የከበረ ጥሩ ናርዶስ ሽቱ የመላበት የአልባስጥሮስ ቢልቃጥ ይዛ መጣች፤ ቢልቃጡንም ሰብራ በራሱ ላይ አፈሰሰችው። 4አንዳንዶችም። ይህ የሽቱ ጥፋት ለምንድር ነው? 5ይህ ሽቱ ከሦስት መቶ ዲናር በሚበልጥ ዋጋ ተሽጦ ለድሆች ሊሰጥ ይቻል ነበርና ብለው በራሳቸው ይቈጡ ነበር፤ እርስዋንም ነቀፉአት። 6ኢየሱስ ግን እንዲህ አለ። ተዉአት፤ ስለ ምን ታደክሙአታላችሁ? መልካም ሥራ ሠርታልኛለች። 7ድሆች ሁልጊዜ ከእናንተ ጋር ይኖራሉና፥ በማናቸውም በወደዳችሁት ጊዜ መልካም ልታደርጉላቸው ትችላላችሁ፥ እኔ ግን ሁልጊዜ ከእናንተ ጋር አልኖርም። 8የተቻላትን አደረገች፤ አስቀድማ ለመቃብሬ ሥጋዬን ቀባችው። 9እውነት እላችኋለሁ፥ ይህ ወንጌል በዓለሙ ሁሉ በሚሰበክበት በማናቸውም ስፍራ፥ እርስዋ ያደረገችው ደግሞ ለእርስዋ መታሰቢያ ሊሆን ይነገራል።

10ከአሥራ ሁለቱም አንዱ የአስቆሮቱ ይሁዳ አሳልፎ ሊሰጠው ወደ ካህናት አለቆች ሄደ። 11ሲሰሙም ደስ አላቸው ብርም ይሰጡት ዘንድ ተስፋ ሰጡት። በሚመች ጊዜም እንዴት አድርጎ አሳልፎ እንዲሰጠው ይፈልግ ነበር።

12ፋሲካን በሚያርዱበት በቂጣ በዓል መጀመሪያ ቀን ደቀ መዛሙርቱ። ፋሲካን ትበላ ዘንድ ወዴት ሄደን ልናሰናዳ ትወዳለህ? አሉት። 13ከደቀ መዛሙርቱም ሁለት ላከ እንዲህም አላቸው። ወደ ከተማ ሂዱ፥ ማድጋ ውኃ የተሸከመ ሰውም ይገናኛችኋል፤ 14ተከተሉት፥ የሚገባበትንም የቤቱን ጌታ። መምህሩ። ከደቀ መዛሙርቴ ጋር ፋሲካን የምበላበት የእንግዳ ቤት ወዴት ነው? ይላል በሉት። 15እርሱም በደርብ ላይ ያለውን የተሰናዳና የተነጠፈ ታላቅ አዳራሽ ያሳያችኋል፤ 16በዚያም አሰናዱልን። ደቀ መዛሙርቱም ወጡ ወደ ከተማም ሄደው እንዳላቸው አገኙ፥ ፋሲካንም አሰናዱ።

17በመሸም ጊዜ ከአሥራ ሁለቱ ጋር መጣ። 18ተቀምጠውም ሲበሉ ኢየሱስ። እውነት እላችኋለሁ፥ ከእናንተ አንዱ፥ እርሱም ከእኔ ጋር የሚበላው አሳልፎ ይሰጠኛል አለ። 19እነርሱም ያዝኑ፥ እያንዳንዳቸውም። እኔ እሆንን? ይሉት ጀመር። 20እርሱም መልሶ። ከአሥራ ሁለቱ አንዱ ከእኔ ጋር ወደ ወጭቱ እጁን የሚያጠልቀው ነው። 21የሰው ልጅስ ስለ እርሱ እንደ ተጻፈ ይሄዳል፤ ነገር ግን የሰው ልጅ አልፎ ለሚሰጥበት ለዚያ ሰው ወዮለት፤ ያ ሰው ባልተወለደ ይሻለው ነበር አላቸው።

22ሲበሉም ኢየሱስ እንጀራን አንሥቶ ባረከ ቈርሶም ሰጣቸውና። እንካችሁ፤ ይህ ሥጋዬ ነው አለ። 23ጽዋንም አንሥቶ አመስግኖም ሰጣቸው፥ ሁሉም ከእርሱ ጠጡ። 24እርሱም። ይህ ስለ ብዙዎች የሚፈስ የአዲስ ኪዳን ደሜ ነው። 25እውነት እላችኋለሁ፥ በእግዚአብሔር መንግሥት ከወይኑ ፍሬ አዲሱን እስከምጠጣበት እስከዚያ ቀን ድረስ ደግሞ አልጠጣውም አላቸው።

26መዝሙርም ከዘመሩ በኋላ ወደ ደብረ ዘይት ወጡ።

27ኢየሱስም። በዚች ሌሊት ሁላችሁ በእኔ ትሰናከላላችሁ፤ እረኛዉን እመታለሁ በጎችም ይበተናሉ የሚል ተጽፎአልና። 28ነገር ግን ከተነሣሁ በኋላ ወደ ገሊላ እቀድማችኋለሁ አላቸው። 29ጴጥሮስም። ሁሉም ቢሰናከሉ እኔ ግን ከቶ አልሰናከልም አለው። 30ኢየሱስም። እውነት እልሃለሁ፥ ዛሬ በዚች ሌሊት ዶሮ ሁለት ጊዜ ሳይጮኽ ሦስት ጊዜ ትክደኛለህ አለው። 31እርሱም ቃሉን አበርትቶ። ከአንተ ጋር የምሞት እንኳ ቢሆን ከቶ አልክድህም አለ። ሁሉም ደግሞ እንደዚሁ አሉ።

32ጌቴሴማኒ ወደምትባልም ስፍራ መጡ፥ ደቀ መዛሙርቱንም። ስጸልይ ሳለሁ፥ በዚህ ተቀመጡ አላቸው። 33ጴጥሮስንና ያዕቆብን ዮሐንስንም ከእርሱ ጋር ወሰደ፤ ሊደነግጥም ሊተክዝም ጀመረና። 34ነፍሴ እስከ ሞት ድረስ እጅግ አዘነች፤ በዚህ ቈዩ ትጉም አላቸው። 35ጥቂትም ወደ ፊት እልፍ ብሎ በምድርም ወድቆ፥ ይቻልስ ቢሆን ሰዓቲቱ ከእርሱ እንድታልፍ ጸለየና። 36አባ አባት ሆይ፥ ሁሉ ይቻልሃል፤ ይህችን ጽዋ ከእኔ ውሰድ፤ ነገር ግን አንተ የምትወደው እንጂ እኔ የምወደው አይሁን አለ። 37መጣም ተኝተውም አገኛቸው፥ ጴጥሮስንም። ስምዖን ሆይ፥ ተኝተሃልን? አንዲት ሰዓት ስንኳ ልትተጋ አልቻልህምን? 38ወደ ፈተና እንዳትገቡ ትጉ ጸልዩም፤ መንፈስስ ተዘጋጅታለች፥ ሥጋ ግን ደካማ ነው አለው። 39ደግሞም ሄዶ ያንኑ ቃል ጸለየ። 40ደግሞም መጥቶ ዓይኖቻቸው በእንቅልፍ ከብደው ነበርና ተኝተው አገኛቸው፥ የሚመልሱለትንም አላወቁም። 41ሦስተኛም መጥቶ። እንግዲህስ ተኙ ዕረፉም፤ ይበቃል፤ ሰዓቲቱ ደረሰች፤ እነሆ፥ የሰው ልጅ በኃጢአተኞች እጅ አልፎ ይሰጣል። 42ተነሡ፥ እንሂድ፤ እነሆ፥ አሳልፎ የሚሰጠኝ ቀርቦአል አላቸው።

43ወዲያውም ገና ሲናገር ከአሥራ ሁለቱ አንዱ ይሁዳ መጣ፥ ከእርሱም ጋር ብዙ ሰዎች ሰይፍና ጐመድ ይዘው ከካህናት አለቆችና ከጻፎች ከሽማግሌዎችም ዘንድ መጡ። 44አሳልፎ የሚሰጠውም። የምስመው እርሱ ነው፤ ያዙት ተጠንቅቃችሁም ውሰዱት ብሎ ምልክት ሰጥቶአቸው ነበር። 45መጥቶም ወዲያው ወደ እርሱ ቀረበና። መምህር ሆይ፥ መምህር ሆይ፥ ብሎ ሳመው፤ 46እነርሱም እጃቸውን በእርሱ ላይ ጭነው ያዙት። 47በአጠገብ ከቆሙት ግን አንዱ ሰይፉን መዞ የሊቀ ካህናቱን ባሪያ መታ ጆሮውንም ቈረጠ። 48ኢየሱስም መልሶ። ወንበዴ እንደምትይዙ ሰይፍና ጐመድ ይዛችሁ ልትይዙኝ መጣችሁን? 49በመቅደስ ዕለት ዕለት እያስተማርሁ ከእናንተ ጋር ስኖር አልያዛችሁኝም፤ ነገር ግን መጻሕፍት ይፈጸሙ ዘንድ ይህ ሆነ አላቸው። 50ሁሉም ትተውት ሸሹ።

51ዕርቃኑን በነጠላ የሸፈነ አንድ ጎበዝ ይከተለው ነበር፥ 52ጎበዛዝቱም ያዙት፤ እርሱ ግን ነጠላውን ትቶ ዕራቁቱን ሸሸ።

53ኢየሱስንም ወደ ሊቀ ካህናቱ ወሰዱት፥ የካህናት አለቆችም ሁሉ ሽማግሌዎችም ጻፎችም ተሰበሰቡ። 54ጴጥሮስም እስከ ሊቀ ካህናቱ ግቢ ውስጥ በሩቁ ተከተለው፥ ከሎሌዎችም ጋር ተቀምጦ እሳት ይሞቅ ነበር። 55የካህናት አለቆችም ሸንጎውም ሁሉ እንዲገድሉት በኢየሱስ ላይ ምስክር ይፈልጉ ነበር፥ አላገኙምም፤ 56ብዙዎች በሐሰት ይመሰክሩበት ነበርና፥ ምስክርነታቸው ግን አልተሰማማም። 57ሰዎችም ተነሥተው። እኔ ይህን በእጅ የተሠራውን ቤተ መቅደስ አፈርሰዋለሁ በሦስት ቀንም ሌላውን በእጅ ያልተሠራውን እሠራለሁ ሲል ሰማነው ብለው በሐሰት መሰከሩበት። 58 59ምስክርነታቸውም እንዲሁ እንኳ አልተሰማማም። 60ሊቀ ካህናቱም በመካከላቸው ተነሥቶ። አንዳች አትመልስምን? እነዚህስ በአንተ ላይ የሚመሰክሩብህ ምንድር ነው? ብሎ ኢየሱስን ጠየቀው። 61እርሱ ግን ዝም አለ አንዳችም አልመለሰም። ደግሞ ሊቀ ካህናቱ ጠየቀውና። የቡሩክ ልጅ ክርስቶስ አንተ ነህን? አለው። 62ኢየሱስም። እኔ ነኝ፤ የሰው ልጅም በኃይል ቀኝ ሲቀመጥ በሰማይም ደመና ሲመጣ ታያላችሁ አለ። 63ሊቀ ካህናቱም ልብሱን ቀደደና። ከእንግዲህ ወዲህ ምስክሮችን ምን ያስፈልገናል? 64ስድቡን ሰማችሁ፤ ምን ይመስላችኋል? አለ። እነርሱም ሁሉ። ሞት ይገባዋል ብለው ፈረዱበት። 65አንዳንዶችም ይተፉበት ፊቱንም ሸፍነው ይጐስሙትና። ትንቢት ተናገር ይሉት ጀመር፤ ሎሌዎችም በጥፊ እየመቱ ወሰዱት።

66ጴጥሮስም በግቢ ውስጥ ወደ ታች ሳለ ከሊቀ ካህናቱ ገረዶች አንዲቱ መጣች፥ 67ጴጥሮስም እሳት ሲሞቅ አይታ ተመለከተችውና። አንተ ደግሞ ከናዝሬቱ ከኢየሱስ ጋር ነበርህ አለችው። 68እርሱ ግን። የምትዪውን አላውቅም አላስተውልምም ብሎ ካደ። ወደ ውጭም ወደ ደጅ ወጣ፤ ዶሮም ጮኸ። 69ገረዲቱም አይታው በዚያ ለቆሙት። ይህም ከእነርሱ ወገን ነው ስትል ሁለተኛ ትነግራቸው ጀመር። 70እርሱም ደግሞ ካደ። ጥቂት ቈይተውም በዚያ የቆሙት ዳግመኛ ጴጥሮስን። የገሊላ ሰው ነህና ከእነርሱ ወገን በእውነት ነህ አሉት። 71እርሱ ግን። ይህን የምትሉትን ሰው አላውቀውም ብሎ ይረገምና ይምል ጀመር። ወዲያውም ዶሮ ሁለተኛ ጮኸ። 72ጴጥሮስንም ኢየሱስ። ዶሮ ሁለት ጊዜ ሳይጮኽ ሦስት ጊዜ ትክደኛለህ ያለው ቃል ትዝ አለው፤ ነገሩንም አስቦ አለቀሰ።

Revised Amharic Bible in XML (2003). Printed version by United Bible Societies (C)1962. E-Text in transliterated ASCII format by Lapsley/Brooks Foundation 1994. Unicode UTF-8 transformation and XML-tagging by Dirk Röckmann 2003 (www.nt-text.net). -- With kind permission of the Bible Society of Ethiopia. Every non-commercial work using this data in any form must fully include this copyright statement! Every commercial use of parts or the complete data in any form needs written permission of the Bible Society of Ethiopia!

Bible Hub

Mark 13
Top of Page
Top of Page