የሉቃስ ወንጌል 7
Amharic NT

1ቃሉን ሁሉ በሕዝብ ጆሮዎች በጨረሰ ጊዜ ወደ ቅፍርናሆም ገባ።

2አንድ የመቶ አለቃም ነበረ፤ የሚወደውም ባሪያው ታሞ ሊሞት ቀርቦ ነበር። 3ስለ ኢየሱስም በሰማ ጊዜ የአይሁድን ሽማግሎች ወደ እርሱ ላከና መጥቶ ባሪያውን እንዲያድን ለመነው። 4እነርሱም ወደ ኢየሱስ መጥተው። ይህን ልታደርግለት ይገባዋል፤ 5ሕዝባችንን ይወዳልና ምኵራብም ራሱ ሠርቶልናል ብለው አጽንተው ለመኑት። 6ኢየሱስም ከእነርሱ ጋር ሄደ። አሁንም ወደ ቤቱ በቀረበ ጊዜ የመቶው አለቃ ወዳጆቹን ወደ እርሱ ላከ፤ አለውም። ጌታ ሆይ በቤቴ ጣራ በታች ልትገባ አይገባኝምና አትድከም፤ 7ስለዚህም ወደ አንተ ልመጣ እንዲገባኝ ሰውነቴን አልቈጠርሁትም፤ ነገር ግን ቃል ተናገር፥ ብላቴናዬም ይፈወሳል። 8እኔ ደግሞ ከሌሎች በታች የምገዛ ሰው ነኝ፥ ከእኔም በታች ወታደሮች አሉኝ፥ አንዱንም። ሂድ ብለው ይሄዳል፥ ሌላውንም። ና ብለው ይመጣል፥ ባሪያዬንም። ይህን አድርግ ብለው ያደርጋል። 9ኢየሱስም ይህን ሰምቶ በእርሱ ተደነቀ፥ ዘወርም ብሎ ለተከተሉት ሕዝብ። እላችኋለሁ፥ በእስራኤልስ እንኳ እንዲህ ያለ ትልቅ እምነት አላገኘሁም አላቸው። 10የተላኩትም ወደ ቤት ተመልሰው ባሪያውን ባለ ጤና ሆኖ አገኙት።

11በነገውም ናይን ወደምትባል ወደ አንዲት ከተማ ሄደ፥ ደቀ መዛሙርቱም ብዙ ሕዝብም ከእርሱ ጋር አብረው ሄዱ። 12ወደ ከተማይቱም በር በቀረበ ጊዜ፥ እነሆ፥ የሞተ ሰው ተሸክመው አወጡ፤ እርሱም ለእናቱ አንድ ልጅ ነበረ፥ እርስዋም መበለት ነበረች፥ ብዙም የከተማ ሕዝብ ከእርስዋ ጋር አብረው ነበሩ። 13ጌታም ባያት ጊዜ አዘነላትና። አታልቅሽ አላት። 14ቀርቦም ቃሬዛውን ነካ፥ የተሸከሙትም ቆሙ፤ አለውም። አንተ ጐበዝ፥ እልሃለሁ፥ ተነሣ። 15የሞተውም ቀና ብሎ ተቀመጠ ሊናገርም ጀመረ፥ ለእናቱም ሰጣት። 16ሁሉንም ፍርሃት ያዛቸውና። ታላቅ ነቢይ በእኛ መካከል ተነሥቶአል፥ ደግሞ። እግዚአብሔር ሕዝቡን ጐበኘ እያሉ እግዚአብሔርን አመሰገኑ። 17ይህም ዝና ስለ እርሱ በይሁዳ ሁሉ በዙሪያውም ባለች አገር ሁሉ ወጣ።

18ደቀ መዛሙርቱም ለዮሐንስ እነዚህን ሁሉ አወሩ። 19ዮሐንስም ከደቀ መዛሙርቱ ሁለት ወደ እርሱ ጠርቶ። የሚመጣው አንተ ነህን ወይስ ሌላውን እንጠብቅ? ብሎ ወደ ኢየሱስ ላከ። 20ሰዎቹም ወደ እርሱ መጥተው። መጥምቁ ዮሐንስ። የሚመጣው አንተ ነህን ወይስ ሌላውን እንጠብቅ? ብሎ ወደ አንተ ላከን አሉት። 21በዚያች ሰዓት ከደዌና ከሥቃይ ከክፉዎች መናፍስትም ብዙዎችን ፈወሰ፥ ለብዙ ዕውሮችም ማየትን ሰጠ። 22ኢየሱስም መልሶ። ሄዳችሁ ያያችሁትን የሰማችሁትንም ለዮሐንስ አውሩለት፤ ዕውሮች ያያሉ፥ አንካሶችም ይሄዳሉ፥ ለምጻሞችም ይነጻሉ፥ ደንቆሮዎችም ይሰማሉ፥ ሙታንም ይነሣሉ፥ ለድሆችም ወንጌል ይሰበካል፤ 23በእኔም የማይሰናከለው ሁሉ ብፁዕ ነው አላቸው።

24የዮሐንስ መልክተኞችም ከሄዱ በኋላ፥ ለሕዝቡ ስለ ዮሐንስ ይናገር ጀመር እንዲህም አለ። ምን ልታዩ ወደ ምድረ በዳ ወጣችሁ? ነፋስ የሚወዘውዘውን ሸምበቆን? ወይስ ምን ልታዩ ወጣችሁ? 25ቀጭን ልብስ የለበሰውን ሰውን? እነሆ፥ ጌጠኛ ልብስ የሚለብሱና በቅምጥልነት የሚኖሩ በነገሥታት ቤት አሉ። 26ወይስ ምን ልታዩ ወጣችሁ? ነቢይን? አዎን እላችኋለሁ፥ ከነቢይም የሚበልጠውን።

27እነሆ፥ መንገድህን በፊትህ የሚጠርግ መልክተኛዬን በፊትህ እልካለሁ ተብሎ የተጻፈለት ይህ ነው።

28እላችኋለሁ፥ ከሴቶች ከተወለዱት መካከል ከመጥምቁ ዮሐንስ የሚበልጥ ማንም የለም፤ በእግዚአብሔር መንግሥት ግን ከሁሉ የሚያንሰው ይበልጠዋል። 29የሰሙትም ሕዝብ ሁሉ ቀራጮች እንኳ ሳይቀሩ በዮሐንስ ጥምቀት ተጠምቀው እግዚአብሔርን አጸደቁ፤ 30ፈሪሳውያንና ሕግ አዋቂዎች ግን በእርሱ ስለ አልተጠመቁ የእግዚአብሔርን ምክር ከራሳቸው ጣሉ።

31እንግዲህ የዚችን ትውልድ ሰዎች በምን አስመስላቸዋለሁ? ማንንስ ይመስላሉ? 32በገበያ የሚቀመጡትን ልጆች ይመስላሉ፥ እርስ በርሳቸውም እየተጠራሩ። እንቢልታ ነፋንላችሁ አልዘፈናችሁምም፤ ሙሾ አወጣንላችሁ አላለቀሳችሁምም ይላል። 33መጥምቁ ዮሐንስ እንጀራ ሳይበላ የወይን ጠጅም ሳይጠጣ መጥቶ ነበርና። ጋኔን አለበት አላችሁት። 34የሰው ልጅ እየበላና እየጠጣ መጥቶአልና። እነሆ፥ በላተኛና የወይን ጠጅ ጠጭ፥ የቀራጮችና የኃጢአተኞች ወዳጅ አላችሁት። 35ጥበብም ለልጆችዋ ሁሉ ጸደቀች።

36ከፈሪሳውያንም አንድ ከእርሱ ጋር ይበላ ዘንድ ለመነው፤ በፈሪሳዊው ቤትም ገብቶ በማዕድ ተቀመጠ። 37እነሆም በዚያች ከተማ ኃጢአተኛ የነበረች አንዲት ሴት፤ በፈሪሳዊው ቤት በማዕድ እንደ ተቀመጠ ባወቀች ጊዜ፥ ሽቱ የሞላበት የአልባስጥሮስ ቢልቃጥ አመጣች። 38በስተ ኋላውም በእግሩ አጠገብ ቆማ እያለቀሰች በእንባዋ እግሩን ታርስ ጀመረች፥ በራስ ጠጕርዋም ታብሰው እግሩንም ትስመው ሽቱም ትቀባው ነበረች። 39የጠራው ፈሪሳዊም አይቶ። ይህስ ነቢይ ቢሆን፥ ይህች የምትዳስሰው ሴት ማን እንደ ሆነች እንዴትስ እንደ ነበረች ባወቀ ነበር፥ ኃጢአተኛ ናትና ብሎ በልቡ አሰበ።

40ኢየሱስም መልሶ። ስምዖን ሆይ፥ የምነግርህ ነገር አለኝ አለው። እርሱም። መምህር ሆይ፥ ተናገር አለ። 41ለአንድ አበዳሪ ሁለት ተበዳሪዎች ነበሩት በአንዱ አምስት መቶ ዲናር ነበረበት በሁለተኛውም አምሳ። 42የሚከፍሉትም ቢያጡ ለሁለቱም ተወላቸው። እንግዲህ ከእነርሱ አብልጦ የሚወደው ማንኛው ነው? 43ስምዖንም መልሶ። ብዙ የተወለቱ ይመስለኛል አለ። እርሱም። በእውነት ፈረድህ አለው። 44ወደ ሴቲቱም ዘወር ብሎ ስምዖንን እንዲህ አለው። ይህችን ሴት ታያለህን? እኔ ወደ ቤትህ ገባሁ፥ ውኃ ስንኳ ለእግሬ አላቀረብህልኝም፤ እርስዋ ግን በእንባዋ እግሬን አራሰች በጠጕርዋም አበሰች። 45አንተ አልሳምኸኝም፤ እርስዋ ግን ከገባሁ ጀምራ እግሬን ከመሳም አላቋረጠችም። 46አንተ ራሴን ዘይት አልቀባኸኝም፤ እርስዋ ግን እግሬን ሽቱ ቀባች። 47ስለዚህ እልሃለሁ፥ እጅግ ወዳለችና ብዙ ያለው ኃጢአትዋ ተሰርዮላታል፤ ጥቂት ግን የሚሰረይለት ጥቂት ይወዳል። 48እርስዋንም። ኃጢአትሽ ተሰርዮልሻል አላት። 49ከእርሱም ጋር በማዕድ ተቀምጠው የነበሩት በልባቸው። ኃጢአትን እንኳ የሚያስተሰርይ ይህ ማን ነው? ይሉ ጀመር። 50ሴቲቱንም። እምነትሽ አድኖሻል፤ በሰላም ሂጂ አላት።

Revised Amharic Bible in XML (2003). Printed version by United Bible Societies (C)1962. E-Text in transliterated ASCII format by Lapsley/Brooks Foundation 1994. Unicode UTF-8 transformation and XML-tagging by Dirk Röckmann 2003 (www.nt-text.net). -- With kind permission of the Bible Society of Ethiopia. Every non-commercial work using this data in any form must fully include this copyright statement! Every commercial use of parts or the complete data in any form needs written permission of the Bible Society of Ethiopia!

Bible Hub

Luke 6
Top of Page
Top of Page