ወደ ዕብራውያን 8
Amharic NT

1ከተናገርነውም ዋና ነገሩ ይህ ነው፤ በሰማያት በግርማው ዙፋን ቀኝ የተቀመጠ እንዲህ ያለ ሊቀ ካህናት አለን፤ 2እርሱም የመቅደስና የእውነተኛይቱ ድንኳን አገልጋይ ነው፥ እርስዋም በሰው ሳይሆን በጌታ የተተከለች ናት። 3ሊቀ ካህናት ሁሉ መባንና መሥዋዕትን ሊያቀርብ ይሾማልና፤ ስለዚህም ለዚህ ደግሞ የሚያቀርበው አንዳች ሊኖረው የግድ ነው። 4እንግዲህ በምድር ቢኖርስ፥ እንደ ሕግ መባን የሚያቀርቡት ስላሉ፥ ካህን እንኳ ባልሆነም፤ 5እነርሱም ሙሴ ድንኳኒቱን ሊሠራ ሳለ እንደ ተረዳ፥ ለሰማያዊ ነገር ምሳሌና ጥላ የሚሆነውን ያገለግላሉ። በተራራው እንደ ተገለጠልህ ምሳሌ ሁሉን ታደርግ ዘንድ ተጠንቀቅ ብሎት ነበርና። 6አሁን ግን በሚሻል ተስፋ ቃል በተመሠረተ በሚሻል ኪዳን ደግሞ መካከለኛ እንደሚሆን በዚያ ልክ እጅግ የሚሻል አገልግሎት አግኝቶአል።

7ፊተኛው ኪዳን ነቀፋ ባይኖረው፥ ለሁለተኛው ስፍራ ባልተፈለገም ነበር።

8እነርሱን እየነቀፈ ይላቸዋልና። እነሆ፥ ከእስራኤል ቤትና ከይሁዳ ቤት ጋር አዲስ ኪዳን የምገባበት ወራት ይመጣል ይላል ጌታ፤

9ከግብፅ አገር አወጣቸው ዘንድ እጃቸውን በያዝሁበት ቀን ከአባቶቻቸው ጋር እንደገባሁት ኪዳን አይደለም፤ እነርሱ በኪዳኔ አልጸኑምና፥ እኔም ቸል አልኋቸው ይላል ጌታ።

10ከዚያ ወራት በኋላ ከእስራኤል ቤት ጋር የምገባው ቃል ኪዳን ይህ ነውና ይላል ጌታ፤ ሕጌን በልቡናቸው አኖራለሁ በልባቸውም እጽፈዋለሁ፥ እኔም አምላክ እሆንላቸዋለሁ እነርሱም ሕዝብ ይሆኑልኛል።

11እያንዳንዱም ጐረቤቱን እያንዳንዱም ወንድሙን። ጌታን እወቅ ብሎ አያስተምርም ከታናሹ ጀምሮ እስከ ታላቁ ድረስ ሁሉ ያውቁኛልና።

12ዓመፃቸውን እምራቸዋለሁና፥ ኃጢአታቸውንም ደግሜ አላስብም።

13አዲስ በማለቱ ፊተኛውን አስረጅቶአል፤ አሮጌና ውራጅ የሆነውስ ሊጠፋ ቀርቦአል።

Revised Amharic Bible in XML (2003). Printed version by United Bible Societies (C)1962. E-Text in transliterated ASCII format by Lapsley/Brooks Foundation 1994. Unicode UTF-8 transformation and XML-tagging by Dirk Röckmann 2003 (www.nt-text.net). -- With kind permission of the Bible Society of Ethiopia. Every non-commercial work using this data in any form must fully include this copyright statement! Every commercial use of parts or the complete data in any form needs written permission of the Bible Society of Ethiopia!

Bible Hub

Hebrews 7
Top of Page
Top of Page