ወደ ኤፌሶን ሰዎች 1

<< ወደ ኤፌሶን ሰዎች 1 >>
Ephesians 1 Amharic NT
 

1 በእግዚአብሔር ፈቃድ የኢየሱስ ክርስቶስ ሐዋርያ የሆነ ጳውሎስ፥ በኤፌሶን ላሉት ቅዱሳን በክርስቶስ ኢየሱስም ላሉት ምእመናን፤ 2 ከእግዚአብሔር ከአባታችን ከጌታም ከኢየሱስ ክርስቶስ ጸጋና ሰላም ለእናንተ ይሁን።

3 በክርስቶስ በሰማያዊ ስፍራ በመንፈሳዊ በረከት ሁሉ የባረከን የጌታችን የኢየሱስ ክርስቶስ አምላክና አባት ይባረክ። 4 ዓለም ሳይፈጠር፥ በፊቱ ቅዱሳንና ነውር የሌለን በፍቅር እንሆን ዘንድ በክርስቶስ መረጠን። 5 በበጎ ፈቃዱ እንደ ወደደ፥ በኢየሱስ ክርስቶስ ሥራ ለእርሱ ልጆች ልንሆን አስቀድሞ ወሰነን። 6 በውድ ልጁም እንዲያው የሰጠን የጸጋው ክብር ይመሰገን ዘንድ ይህን አደረገ። 7 በውድ ልጁም፥ እንደ ጸጋው ባለ ጠግነት መጠን፥ በደሙ የተደረገ ቤዛነታችንን አገኘን እርሱም የበደላችን ስርየት። 8 ጸጋውንም በጥበብና በአእምሮ ሁሉ አበዛልን። 9 በክርስቶስ ለማድረግ እንደ ወደደ እንደ አሳቡ፥ የፈቃዱን ምሥጢር አስታውቆናልና፤ 10 በዘመን ፍጻሜ ይደረግ ዘንድ ያለው አሳቡም በሰማይና በምድር ያለውን ሁሉ በክርስቶስ ለመጠቅለል ነው። 11 እንደ ፈቃዱ ምክር ሁሉን የሚሠራ እንደ እርሱ አሳብ፥ አስቀድመን የተወሰንን በክርስቶስ ደግሞ ርስትን ተቀበልን። 12 ይኸውም፥ በክርስቶስ አስቀድመን ተስፋ ያደረግን እኛ ለክብሩ ምስጋና እንሆን ዘንድ ነው። 13 እናንተም ደግሞ የእውነትን ቃል፥ ይኸውም የመዳናችሁን ወንጌል፥ ሰምታችሁ ደግሞም በክርስቶስ አምናችሁ፥ በተስፋው መንፈስ በመንፈስ ቅዱስ ታተማችሁ፤ 14 እርሱም የርስታችን መያዣ ነው፥ ለእግዚአብሔር ያለውን ሁሉ እስኪዋጅ ድረስ፥ ይህም ለክብሩ ምስጋና ይሆናል።

15 ስለዚህ እኔ ደግሞ በእናንተ ዘንድ ስለሚሆን በጌታ በኢየሱስ ስለ ማመንና ለቅዱሳን ሁሉ ስለሚሆን መውደድ ሰምቼ፥ 16 ስለ እናንተ እያመሰገንሁ ስጸልይ ስለ እናንተ ማሳሰብን አልተውም፤ 17 የክብር አባት የጌታችን የኢየሱስ ክርስቶስ አምላክ እርሱን በማወቅ የጥበብንና የመገለጥን መንፈስ እንዲሰጣችሁ እለምናለሁ። 18 ይህም የልባችሁ ዓይኖች ሲበሩ የመጥራቱ ተስፋ ምን እንዲሆን በቅዱሳንም ዘንድ ያለው የርስት ክብር ባለ ጠግነት ምን እንዲሆን ለምናምን ከሁሉ የሚበልጥ የኃይሉ ታላቅነት ምን እንዲሆን ታውቁ ዘንድ ነው፤ 19  20 ክርስቶስንም ከሙታን ሲያስነሣው ከአለቅነትና ከሥልጣንም ከኃይልም ከጌትነትም ሁሉ በላይና በዚህ ዓለም ብቻ ሳይሆን ነገር ግን ሊመጣ ባለው ዓለም ደግሞ ከሚጠራው ስም ሁሉ በላይ በሰማያዊ ስፍራ በቀኙ ሲያስቀምጠው በክርስቶስ ባደረገው ሥራ የብርታቱ ጉልበት ይታያል፤ 21  22 ሁሉንም ከእግሩ በታች አስገዛለት ከሁሉ በላይም ራስ እንዲሆን ለቤተ ክርስቲያን ሰጠው። 23 እርስዋም አካሉና ሁሉን በሁሉ የሚሞላ የእርሱ ሙላቱ ናት።


<< Ephesians 1 >>
Revised Amharic Bible in XML (2003). Printed version by United Bible Societies (C)1962. E-Text in transliterated ASCII format by Lapsley/Brooks Foundation 1994. Unicode UTF-8 transformation and XML-tagging by Dirk Röckmann 2003 (www.nt-text.net). -- With kind permission of the Bible Society of Ethiopia. Every non-commercial work using this data in any form must fully include this copyright statement! Every commercial use of parts or the complete data in any form needs written permission of the Bible Society of Ethiopia!

Biblos.com Online Bible