ወደ ቆላስይስ ሰዎች 3

<< ወደ ቆላስይስ ሰዎች 3 >>
Colossians 3 Amharic NT
 

1 እንግዲህ ከክርስቶስ ጋር ከተነሣችሁ፥ ክርስቶስ በእግዚአብሔር ቀኝ ተቀምጦ ባለበት በላይ ያለውን እሹ። 2 በላይ ያለውን አስቡ እንጂ በምድር ያለውን አይደለም። 3 ሞታችኋልና፥ ሕይወታችሁም በእግዚአብሔር ከክርስቶስ ጋር ተሰውሮአልና። 4 ሕይወታችሁ የሆነ ክርስቶስ በሚገለጥበት ጊዜ፥ በዚያን ጊዜ እናንተ ደግሞ ከእርሱ ጋር በክብር ትገለጣላችሁ።

5 እንግዲህ በምድር ያሉቱን ብልቶቻችሁን ግደሉ፥ እነዚህም ዝሙትና ርኵሰት ፍትወትም ክፉ ምኞትም ጣኦትንም ማምለክ የሆነ መጎምጀት ነው። 6 በእነዚህም ጠንቅ የእግዚአብሔር ቍጣ በማይታዘዙ ልጆች ላይ ይመጣል። 7 እናንተም ደግሞ ትኖሩባቸው በነበራችሁ ጊዜ፥ በፊት በእነዚህ ተመላለሳችሁ። 8 አሁን ግን እናንተ ደግሞ ቍጣንና ንዴትን ክፋትንም፥ ከአፋችሁም ስድብን የሚያሳፍርንም ንግግር እነዚህን ሁሉ አስወግዱ። 9 እርስ በርሳችሁ ውሸት አትነጋገሩ፥ አሮጌውን ሰው ከሥራው ጋር ገፋችሁታልና፥ 10 የፈጠረውንም ምሳሌ እንዲመስል እውቀትን ለማግኘት የሚታደሰውን አዲሱን ሰው ለብሳችሁታል። 11 በዚያም የግሪክ ሰው አይሁዳዊም የተገረዘም ያልተገረዘም አረማዊም እስኩቴስም ባሪያም ጨዋ ሰውም መሆን አልተቻለም፥ ነገር ግን ክርስቶስ ሁሉ ነው፥ በሁሉም ነው።

12 እንግዲህ እንደ እግዚአብሔር ምርጦች ቅዱሳን ሆናችሁ የተወደዳችሁም ሆናችሁ፥ ምሕረትን፥ ርኅራኄን፥ ቸርነትን፥ ትህትናን፥ የዋህነትን፥ ትዕግሥትን ልበሱ። 13 እርስ በርሳችሁ ትዕግሥትን አድርጉ፥ ማንም በባልንጀራው ላይ የሚነቅፈው ነገር ካለው፥ ይቅር ተባባሉ። ክርስቶስ ይቅር እንዳላችሁ እናንተ ደግሞ እንዲሁ አድርጉ። 14 በእነዚህም ሁሉ ላይ የፍጻሜ ማሰሪያ የሆነውን ፍቅርን ልበሱት። 15 በአንድ አካልም የተጠራችሁለት ደግሞ የክርስቶስ ሰላም በልባችሁ ይግዛ። የምታመሰግኑም ሁኑ። 16 የእግዚአብሔር ቃል በሙላት ይኑርባችሁ። በጥበብ ሁሉ እርስ በርሳችሁ አስተምሩና ገሥጹ። በመዝሙርና በዝማሬ በመንፈሳዊም ቅኔ በጸጋው በልባችሁ ለእግዚአብሔር ዘምሩ። 17 እግዚአብሔር አብን በእርሱ እያመሰገናችሁ፥ በቃል ቢሆን ወይም በሥራ የምታደርጉትን ሁሉ በጌታ በኢየሱስ ስም አድርጉት።

18 ሚስቶች ሆይ፥ በጌታ እንደሚገባ ለባሎቻችሁ ተገዙ። 19 ባሎች ሆይ፥ ሚስቶቻችሁን ውደዱ መራራም አትሁኑባቸው። 20 ልጆች ሆይ፥ ይህ ለጌታ ደስ የሚያሰኝ ነውና በሁሉ ለወላጆቻችሁ ታዘዙ። 21 አባቶች ሆይ፥ ልባቸው እንዳይዝል ልጆቻችሁን አታበሳጩአቸው።

22 ባሪያዎች ሆይ፥ በቅን ልብ ጌታን እየፈራችሁ እንጂ፥ ለሰው ደስ እንደምታሰኙ ለታይታ የምትገዙ ሳትሆኑ፥ በሥጋ ጌቶቻችሁ ለሆኑ በሁሉ ታዘዙ። 23 ለሰው ሳይሆን ለጌታ እንደምታደርጉ፥ የምታደርጉትን ሁሉ በትጋት አድርጉት፥ 24 ከጌታ የርስትን ብድራት እንድትቀበሉ ታውቃላችሁና። የምታገለግሉት ጌታ ክርስቶስ ነውና። 25 የሚበድልም የበደለውን በብድራት ይቀበላል፥ ለሰው ፊትም አድልዎ የለም።


<< Colossians 3 >>
Revised Amharic Bible in XML (2003). Printed version by United Bible Societies (C)1962. E-Text in transliterated ASCII format by Lapsley/Brooks Foundation 1994. Unicode UTF-8 transformation and XML-tagging by Dirk Röckmann 2003 (www.nt-text.net). -- With kind permission of the Bible Society of Ethiopia. Every non-commercial work using this data in any form must fully include this copyright statement! Every commercial use of parts or the complete data in any form needs written permission of the Bible Society of Ethiopia!

Biblos.com Online Bible