የሐዋርያት ሥራ 3
Amharic NT

1ጴጥሮስና ዮሐንስም በጸሎት ጊዜ በዘጠኝ ሰዓት ወደ መቅደስ ይወጡ ነበር። 2ወደ መቅደስም ከሚገቡት ምጽዋት ይለምን ዘንድ፥ ሰዎች ተሸክመው መልካም በሚሉአት በመቅደስ ደጅ በየቀኑ ያስቀምጡት የነበሩ ከእናቱ ማኅፀን ጀምሮ አንካሳ የሆነ አንድ ሰው ነበረ። 3እርሱም ጴጥሮስና ዮሐንስ ወደ መቅደስ ሊገቡ እንዳላቸው ባየ ጊዜ፥ ምጽዋትን ለመናቸው። 4ጴጥሮስም ከዮሐንስ ጋር ትኵር ብሎ ወደ እርሱ ተመልክቶ። ወደ እኛ ተመልከት አለው። 5እርሱም አንድ ነገር ከእነርሱ እንዲቀበል ሲጠብቅ ወደ እነርሱ ተመለከተ። 6ጴጥሮስ ግን። ብርና ወርቅ የለኝም፤ ይህን ያለኝን ግን እሰጥሃለሁ፤ በናዝሬቱ በኢየሱስ ክርስቶስ ስም ተነሣና ተመላለስ አለው። 7በቀኝ እጁም ይዞ አስነሣው፤ በዚያን ጊዜም እግሩና ቍርጭምጭምቱ ጸና፥ 8ወደ ላይ ዘሎም ቆመ፥ ይመላለስም ጀመር፤ እየተመላለሰም እየዘለለም እግዚአብሔርንም እያመሰገነ ከእነርሱ ጋር ወደ መቅደስ ገባ። 9ሕዝቡም ሁሉ እግዚአብሔርን እያመሰገነ ሲመላለስ አዩት፤ 10መልካምም በሚሉአት በመቅደስ ደጅ ስለ ምጽዋት ተቀምጦ የነበረው እርሱ እንደ ሆነ አወቁት፤ በእርሱም ከሆነው የተነሣ መደነቅና መገረም ሞላባቸው።

11እርሱም ጴጥሮስንና ዮሐንስን ይዞ ሳለ፥ ሕዝቡ ሁሉ እየተደነቁ የሰሎሞን ደጅ መመላለሻ በሚባለው አብረው ወደ እነርሱ ሮጡ። 12ጴጥሮስም አይቶ ለሕዝቡ እንዲህ ሲል መለሰ። የእስራኤል ሰዎች ሆይ፥ በዚህ ስለ ምን ትደነቃላችሁ? ወይስ በገዛ ኃይላችን ወይስ እግዚአብሔርን በመፍራታችን ይህ ይመላለስ ዘንድ እንዳደረግነው ስለ ምን ትኵር ብላችሁ ታዩናላችሁ? 13የአብርሀምና የይስሐቅ የያዕቆብም አምላክ፥ የአባቶቻችን አምላክ፥ እናንተ አሳልፋችሁ የሰጣችሁትንና ሊፈታው ቈርጦ ሳለ በጲላጦስ ፊት የካዳችሁትን ብላቴናውን ኢየሱስን አከበረው። 14እናንተ ግን ቅዱሱን ጻድቁንም ክዳችሁ ነፍሰ ገዳዩን ሰው ይሰጣችሁ ዘንድ ለመናችሁ፥ 15የሕይወትንም ራስ ገደላችሁት፤ እርሱን ግን እግዚአብሔር ከሙታን አስነሣው፥ ለዚህም ነገር እኛ ምስክሮች ነን። 16በስሙም በማመን ይህን የምታዩትንና የምታውቁትን የእርሱ ስም አጸናው፥ በእርሱም በኩል የሆነው እምነት በሁላችሁ ፊት ይህን ፍጹም ጤና ሰጠው።

17አሁንም፥ ወንድሞቼ ሆይ፥ እናንተ እንደ አለቆቻችሁ ደግሞ ባለማወቅ እንዳደረጋችሁት አውቄአለሁ፤ 18እግዚአብሔር ግን ክርስቶስ መከራ እንዲቀበል አስቀድሞ በነቢያት ሁሉ አፍ የተናገረውን እንዲሁ ፈጸመው። 19እንግዲህ ከጌታ ፊት የመጽናናት ዘመን እንድትመጣላችሁ አስቀድሞም ለእናንተ የመረጠውን ኢየሱስ ክርስቶስን እንዲልክላችሁ፥ ኃጢአታችሁ ይደመሰስ ዘንድ ንስሐ ግቡ ተመለሱም። 20 21እግዚአብሔር ከጥንት ጀምሮ በቅዱሳን ነቢያቱ አፍ የተናገረው፥ ነገር ሁሉ እስከሚታደስበት ዘመን ድረስ ሰማይ ይቀበለው ዘንድ ይገባልና። 22ሙሴም ለአባቶች። ጌታ አምላክ እኔን እንዳስነሣኝ ነቢይን ከወንድሞቻችሁ ያስነሣላችኋል፤ በሚነግራችሁ ሁሉ እርሱን ስሙት። 23ያንም ነቢይ የማትሰማው ነፍስ ሁሉ ከሕዝብ ተለይታ ትጠፋለች አለ። 24ሁለተኛም ከሳሙኤል ጀምሮ ከእርሱም በኋላ የተናገሩት ነቢያት ሁሉ ደግሞ ስለዚህ ወራት ተናገሩ። 25እናንተ የነቢያት ልጆችና እግዚአብሔር ለአብርሃም። በዘርህ የምድር ወገኖች ሁሉ ይባረካሉ ብሎ፥ ከአባቶቻችን ጋር ያደረገው የኪዳን ልጆች ናችሁ። 26ለእናንተ አስቀድሞ እግዚአብሔር ብላቴናውን አስነሥቶ፥ እያንዳንዳችሁን ከክፋታችሁ እየመለሰ ይባርካችሁ ዘንድ፥ ሰደደው።

Revised Amharic Bible in XML (2003). Printed version by United Bible Societies (C)1962. E-Text in transliterated ASCII format by Lapsley/Brooks Foundation 1994. Unicode UTF-8 transformation and XML-tagging by Dirk Röckmann 2003 (www.nt-text.net). -- With kind permission of the Bible Society of Ethiopia. Every non-commercial work using this data in any form must fully include this copyright statement! Every commercial use of parts or the complete data in any form needs written permission of the Bible Society of Ethiopia!

Bible Hub

Acts 2
Top of Page
Top of Page