የሐዋርያት ሥራ 24
Amharic NT

1ከአምስት ቀንም በኋላ ሊቀ ካህናቱ ሐናንያ ከሽማግሌዎችና ጠርጠሉስ ከሚሉት ከአንድ ጠበቃ ጋር ወረደ፤ እነርሱም ስለ ጳውሎስ ለአገረ ገዡ አመለከቱት። 2በተጠራም ጊዜ ጠርጠሉስ ይከሰው ዘንድ ጀመረ እንዲህ እያለ። ክቡር ፊልክስ ሆይ፥ በአንተ በኩል ብዙ ሰላም ስለምናገኝ ለዚህም ሕዝብ በአሳብህ በየነገሩ በየስፍራውም መልካም መሻሻል ስለሚሆንለት፥ በፍጹም ምስጋና እንቀበለዋለን። 3 4ነገር ግን እጅግ እንዳላቆይህ በቸርነትህ በአጭሩ ትሰማን ዘንድ እለምንሃለሁ። 5ይህ ሰው በሽታ ሆኖ በዓለም ባሉት አይሁድ ሁሉ ሁከት ሲያስነሣ፥ የመናፍቃን የናዝራውያን ወገን መሪ ሆኖ አግኝተነዋልና፤ 6መቅደስንም ደግሞ ሊያረክስ ሲሞክር ያዝነው፥ እንደ ሕጋችንም እንፈርድበት ዘንድ ወደድን። ነገር ግን የሻለቃው ሉስዮስ መጥቶ በብዙ ኃይል ከእጃችን ወሰደው፥ 8ከሳሾቹንም ወደ አንተ ይመጡ ዘንድ አዘዘ፤ አንተም ራስህ እርሱን መርምረህ እኛ ስለምንከስበት ነገር ሁሉ ልታውቅ ትችላለህ። 9አይሁድም ደግሞ። ይህ ነገር እንዲሁ ነው እያሉ ተስማሙ።

10ገዡም በጠቀሰው ጊዜ ጳውሎስ መለሰ እንዲህ ሲል። ከብዙ ዘመን ጀምረህ ለዚህ ሕዝብ አንተ ፈራጅ እንደ ሆንህ አውቃለሁና ደስ እያለኝ ስለ እኔ ነገር እመልሳለሁ፤ 11እሰግድ ዘንድ ወደ ኢየሩሳሌም ከወጣሁ ከአሥራ ሁለት ቀን እንዳይበልጥ ልታውቀው ትችላለህ። 12ከአንድም ስንኳ ስነጋገር ወይም ሕዝብን ስሰበስብ በመቅደስ ቢሆን በምኵራብም ቢሆን በከተማም ቢሆን አላገኙኝም። 13አሁንም ስለሚከሱኝ ያስረዱህ ዘንድ አይችሉም። 14ነገር ግን ይህን እመሰክርልሃለሁ፤ በሕጉ ያለውን በነቢያትም የተጻፉትን ሁሉ አምኜ የአባቶቼን አምላክ እነርሱ ኑፋቄ ብለው እንደሚጠሩት መንገድ አመልካለሁ፤ 15እነዚህም ራሳቸው ደግሞ የሚጠብቁት፥ ጻድቃንም ዓመፀኞችም ከሙታን ይነሡ ዘንድ እንዳላቸው ተስፋ በእግዚአብሔር ዘንድ አለኝ። 16ስለዚህ እኔ ደግሞ በእግዚአብሔርና በሰው ፊት ሁልጊዜ ነውር የሌለባት ሕሊና ትኖረኝ ዘንድ እተጋለሁ። 17ከብዙ ዓመትም በኋላ ለሕዝቤ ምጽዋትና መሥዋዕት አደርግ ዘንድ መጣሁ፤ 18ይህንም ሳደርግ ሳለሁ ሕዝብ ሳይሰበሰብ ሁከትም ሳይሆን በመቅደስ ስነጻ አገኙኝ። 19ነገር ግን በእኔ ላይ ነገር ያላቸው እንደ ሆነ፥ በፊትህ መጥተው ይከሱኝ ዘንድ የሚገባቸው ከእስያ የመጡ አንዳንድ አይሁድ አሉ። 20ወይም በመካከላቸው ቆሜ። ዛሬ ስለ ሙታን መነሣት በፊታችሁ በእኔ ይፈርዱብኛል ብዬ ከጮኽሁት ከዚህ ከአንድ ነገር በቀር፥ በሸንጎ ፊት ቆሜ ሳለሁ በእኔ አንድ ዓመፃ ያገኙ እንደ ሆን እነዚህ ራሳቸው ይናገሩ። 21

22ፊልክስ ግን የመንገዱን ነገር አጥብቆ አውቆአልና። የሻለቃው ሉስዮስ በወረደ ጊዜ ነገራችሁን እቆርጣለሁ ብሎ ወደ ፊት አዘገያቸው። 23የመቶውንም አለቃ ጳውሎስን ሲጠብቅ እንዲያደላለት፥ ከወዳጆቹም ማንም ሲያገለግለው ወይም ወደ እርሱ ሲመጣ እንዳይከለክልበት አዘዘው።

24ከጥቂት ቀንም በኋላ ፊልክስ አይሁዳዊት ከነበረች ድሩሲላ ከሚሉአት ከሚስቱ ጋር መጥቶ ጳውሎስን አስመጣ፥ በኢየሱስ ክርስቶስም ስለ ማመን የሚናገረውን ሰማው። 25እርሱም ስለ ጽድቅና ራስን ስለ መግዛት ስለሚመጣውም ኵነኔ ሲነጋገር ሳለ፥ ፊልክስ ፈርቶ። አሁንስ ሂድ፥ በተመቸኝም ጊዜ ልኬ አስጠራሃለሁ ብሎ መለሰለት። 26ያን ጊዜም ደግሞ እንዲፈታው ጳውሎስ ገንዘብ ይሰጠው ዘንድ ተስፋ አደረገ፤ ስለዚህ ደግሞ ብዙ ጊዜ እያስመጣ ያነጋግረው ነበር። 27ሁለት ዓመትም ከሞላ በኋላ ጶርቅዮስ ፊስጦስ በፊልክስ ፈንታ ተተካ። ፊልክስም አይሁድን ደስ ያሰኝ ዘንድ ወዶ ጳውሎስን እንደ ታሰረ ተወው።

Revised Amharic Bible in XML (2003). Printed version by United Bible Societies (C)1962. E-Text in transliterated ASCII format by Lapsley/Brooks Foundation 1994. Unicode UTF-8 transformation and XML-tagging by Dirk Röckmann 2003 (www.nt-text.net). -- With kind permission of the Bible Society of Ethiopia. Every non-commercial work using this data in any form must fully include this copyright statement! Every commercial use of parts or the complete data in any form needs written permission of the Bible Society of Ethiopia!

Bible Hub

Acts 23
Top of Page
Top of Page