
<< የሐዋርያት ሥራ 20 >> Acts 20 Amharic NT | |
1 ሁከቱም ከቀረ በኋላ ጳውሎስ ደቀ መዛሙርቱን አስመጥቶ መከራቸው፥ ተሰናብቶአቸውም ወደ መቄዶንያ ይሄድ ዘንድ ወጣ።
2 ያንም አገር እያለፈ በብዙ ቃል ከመከራቸው በኋላ ወደ ግሪክ አገር መጣ።
3 በዚያም ሦስት ወር ተቀምጦ ወደ ሶርያ በመርከብ ሊሄድ ባሰበ ጊዜ፥ አይሁድ ሴራ ስላደረጉበት በመቄዶንያ አልፎ ይመለስ ዘንድ ቆረጠ።
4 የሸኙትም የቤርያው ሱሲጳጥሮስ ከተሰሎንቄ ሰዎችም አርስጥሮኮስና ሲኮንዱስ የደርቤኑም ጋይዮስና ጢሞቴዎስ የእስያ ሰዎችም ቲኪቆስ ጥሮፊሞስም ነበሩ፤
5 እነዚህም ወደ ፊታችን አልፈው በጢሮአዳ ቆዩን።
6 እኛ ግን ከቂጣ በዓል ቀን በኋላ ከፊልጵስዩስ በመርከብ ተነሥተን በአምስት ቀን ወደ ጢሮአዳ ወደ እነርሱ ደረስንና በዚያ ሰባት ቀን ተቀመጥን።
7 ከሳምንቱም በመጀመሪያ ቀን እንጀራ ለመቁረስ ተሰብስበን ሳለን፥ ጳውሎስ በነገው ሊሄድ ስላሰበ ከእነርሱ ጋር ይነጋገር ነበር፥ እስከ መንፈቀ ሌሊትም ነገሩን አስረዘመ።
8 ተሰብስበንም በነበርንበት ሰገነት እጅግ መብራት ነበረ።
9 አውጤኪስ የሚሉትም አንድ ጎበዝ በመስኮት ተቀምጦ ታላቅ እንቅልፍ አንቀላፍቶ ነበር፤ ጳውሎስም ነገርን ባስረዘመ ጊዜ እንቅልፍ ከብዶት ከሦስተኛው ደርብ ወደ ታች ወደቀ፥ ሞቶም አነሡት።
10 ጳውሎስም ወርዶ በላዩ ወደቀ፥ አቅፎም። ነፍሱ አለችበትና አትንጫጩ አላቸው።
11 ወጥቶም እንጀራ ቆርሶም በላ፤ ብዙ ጊዜም እስኪነጋ ድረስ ተነጋገረ እንዲህም ሄደ።
12 ብላቴናውንም ደኅና ሆኖ ወሰዱት እጅግም ተጽናኑ።
13 እኛ ግን ጳውሎስን ከዚያ እንቀበለው ዘንድ ስላለን ወደ መርከብ ቀድመን ሄድንና ወደ አሶን ተነሣን፤ እርሱ በመሬት ይሄድ ዘንድ ስላሰበ እንደዚህ አዞ ነበርና።
14 በአሶንም ባገኘን ጊዜ ተቀብለነው ወደ ሚጢሊኒ መጣን፤
15 በማግሥቱም ከዚያ በባሕር ተነሥተን በኪዩ ፊት ለፊት ደረስን፥ በነገውም ወደ ሳሞን ተሻገርን በትሮጊሊዮም አድረን በማግሥቱ ወደ ሚሊጢን መጣን።
16 ጳውሎስ በእስያ እጅግ እንዳይቀመጥ ኤፌሶንን ይተው ዘንድ ቆርጦ ነበርና ቢቻለውም በዓለ ኀምሳን በኢየሩሳሌም ይውል ዘንድ ይቸኩል ነበርና።
17 ከሚሊጢንም ወደ ኤፌሶን ልኮ የቤተክርስቲያንን ሽማግሌዎች አስጠራቸው፤
18 ወደ እርሱም በመጡ ጊዜ እንዲህ አላቸው። ወደ እስያ ከገባሁበት ከመጀመሪያ ቀን ጀምሮ፥ በትሕትና ሁሉና በእንባ ከአይሁድም ሴራ በደረሰብኝ ፈተና ለጌታ እየተገዛሁ ዘመኑን ሁሉ ከእናንተ ጋር እንዴት እንደ ኖርሁ እናንተው ታውቃላችሁ፤
19
20 ወደ እግዚአብሔር ዘንድ ንስሐንና በጌታችን በኢየሱስ ክርስቶስ ማመንን ለአይሁድና ለግሪክ ሰዎች እየመሰከርሁ በጉባኤም በየቤታችሁም አወራሁላችሁና አስተማርኋችሁ እንጂ፥ ከሚጠቅማችሁ ነገር አንዳች ስንኳ አላስቀረሁባችሁም።
21
22 አሁንም፥ እነሆ፥ እኔ በመንፈስ ታስሬ ወደ ኢየሩሳሌም እሄዳለሁ፥ በዚያም የሚያገኘኝ ምን እንደ ሆነ አላውቅም፤
23 ነገር ግን መንፈስ ቅዱስ። እስራትና መከራ ይቆይሃል ብሎ በየከተማው ሁሉ ይመሰክርልኛል።
24 ነገር ግን ሩጫዬንና ከጌታ ከኢየሱስ የተቀበልሁትን አገልግሎት እርሱም የእግዚአብሔርን ጸጋ ወንጌልን መመስከር እፈጽም ዘንድ ነፍሴን በእኔ ዘንድ እንደማትከብር እንደ ከንቱ ነገር እቆጥራለሁ።
25 አሁንም፥ እነሆ፥ እኔ የእግዚአብሔርን መንግሥት እየሰበክሁ በመካከላችሁ የዞርሁ ሁላችሁ ከእንግዲህ ወዲህ ፊቴን እንዳትዩ አውቃለሁ።
26 ስለዚህ እኔ ከሰው ሁሉ ደም ንጹሕ እንደ ሆንሁ ዛሬ በዚች ቀን እመሰክርላችኋለሁ።
27 የእግዚአብሔርን ምክር ሁሉ ነግሬአችኋለሁና፥ ምንም አላስቀረሁባችሁም።
28 በገዛ ደሙ የዋጃትን የእግዚአብሔርን ቤተ ክርስቲያን ትጠብቁአት ዘንድ መንፈስ ቅዱስ እናንተን ጳጳሳት አድርጎ ለሾመባት ለመንጋው ሁሉና ለራሳችሁ ተጠንቀቁ።
29 ከሄድሁ በኋላ ለመንጋው የማይራሩ ጨካኞች ተኩላዎች እንዲገቡባችሁ፥ ደቀ መዛሙርትንም ወደ ኋላቸው ይስቡ ዘንድ ጠማማ ነገርን የሚናገሩ ሰዎች በመካከላችሁ እንዲነሡ እኔ አውቃለሁ።
30
31 ስለዚህ ሦስት ዓመት ሌሊትና ቀን በእንባ እያንዳንዳችሁን ከመገሠጽ እንዳላቋረጥሁ እያሰባችሁ ትጉ።
32 አሁንም ለእግዚአብሔርና ያንጻችሁ ዘንድ በቅዱሳንም ሁሉ መካከል ርስትን ይሰጣችሁ ዘንድ ለሚችል ለጸጋው ቃል አደራ ሰጥቻችኋለሁ።
33 ከማንም ብር ወይም ወርቅ ወይም ልብስ አልተመኘሁም፤
34 እነዚህ እጆቼ በሚያስፈልገኝ ነገር ለእኔና ከእኔ ጋር ላሉት እንዳገለገሉ እናንተ ታውቃላችሁ።
35 እንዲሁ እየደከማችሁ ድውዮችን ልትረዱና እርሱ ራሱ። ከሚቀበል ይልቅ የሚሰጥ ብፁዕ ነው እንዳለ የጌታን የኢየሱስን ቃል ልታስቡ ይገባችሁ ዘንድ በሁሉ አሳየኋችሁ።
36 ይህንም ብሎ ተንበርክኮ ከሁላቸው ጋር ጸለየ።
37 ሁሉም እጅግ አለቀሱ፥ ጳውሎስንም አንገቱን አቅፈው ይስሙት ነበር፤
38 ይልቁንም። ከእንግዲህ ወዲህ ፊቴን አታዩም ስላላቸው ነገር እጅግ አዘኑ። እስከ መርከብም ድረስ ሸኙት።
<< Acts 20 >> Revised Amharic Bible in XML (2003). Printed version by United Bible Societies (C)1962. E-Text in transliterated ASCII format by Lapsley/Brooks Foundation 1994. Unicode UTF-8 transformation and XML-tagging by Dirk Röckmann 2003 (www.nt-text.net). -- With kind permission of the Bible Society of Ethiopia. Every non-commercial work using this data in any form must fully include this copyright statement! Every commercial use of parts or the complete data in any form needs written permission of the Bible Society of Ethiopia!
Biblos.com Online Bible |