የሐዋርያት ሥራ 14
Amharic NT

1በኢቆንዮንም እንደ ቀድሞ ወደ አይሁድ ምኵራብ ገብተው ከአይሁድና ከግሪክ ሰዎች ብዙ እስኪያምኑ ድረስ ተናገሩ። 2ያላመኑት አይሁድ ግን የአሕዛብን ልብ በወንድሞች ላይ አነሣሡ አስከፉም። 3ምልክትና ድንቅ በእጃቸው ይደረግ ዘንድ እየሰጠ ለጸጋው ቃል ስለ መሰከረው ስለ ጌታ ገልጠው እየተናገሩ ረጅም ወራት ተቀመጡ። 4የከተማውም ሕዝብ ተከፍለው እኵሌቶቹ ከአይሁድ እኵሌቶቹም ከሐዋርያት ጋር ሆኑ። 5አሕዛብና አይሁድ ግን ከአለቆቻቸው ጋር ሊያንገላቱአቸውና ሊወግሩአቸው ባሰቡ ጊዜ፥ 6አውቀው ልስጥራንና ደርቤን ወደሚባሉት ወደ ሊቃኦንያ ከተማዎች በእነርሱም ዙሪያ ወዳለው አገር ሸሹ፤ 7በዚያም ወንጌልን ይሰብኩ ነበር።

8በልስጥራንም እግሩ የሰለለ፥ ከእናቱም ማኅፀን ጀምሮ አንካሳ የሆነ፥ ከቶም ሄዶ የማያውቅ አንድ ሰው ተቀምጦ ነበር። 9ይህም ሰው ጳውሎስ ሲናገር ይሰማ ነበር፤ እርሱም ትኵር ብሎ ተመለከተውና ይድን ዘንድ እምነት እንዳለው ባየ ጊዜ፥ 10በታላቅ ድምፅ። ቀጥ ብለህ በእግርህ ቁም አለው። ብድግ ብሎም ተንሥቶ ይመላለስ ነበር። 11ሕዝቡም ጳውሎስ ያደረገውን ባዩ ጊዜ ድምፃቸውን ከፍ አድርገው በሊቃኦንያ ቋንቋ። አማልክት ሰዎችን መስለው ወደ እኛ ወርደዋል አሉ፤ 12በርናባስንም ድያ አሉት፤ ጳውሎስንም እርሱ በመናገር ዋና ስለ ነበረ ሄርሜን አሉት። 13በከተማውም ፊት ቤተ መቅደስ ያለው የድያ ካህን ኮርማዎችንና የአበባን አክሊሎች ወደ ደጃፍ አምጥቶ ከሕዝቡ ጋር ሆኖ ሊሠዋላቸው ወደደ። 14ሐዋርያት በርናባስና ጳውሎስ ግን ይህን በሰሙ ጊዜ ልብሳቸውን ቀደው ወደ ሕዝቡ መካከል እየጮኹ ሮጡ፥ 15እንዲህም አሉ። እናንተ ሰዎች፥ ይህን ስለ ምን ታደርጋላችሁ? እኛ ደግሞ እንደ እናንተ የምንሰማ ሰዎች ነን፥ ከዚህም ከንቱ ነገር ሰማይንና ምድርን ባሕርንም በእነርሱም ያለውን ሁሉ ወደ ፈጠረ ወደ ሕያው እግዚአብሔር ዘወር ትሉ ዘንድ ወንጌልን እንሰብካለን። 16እርሱ ባለፉት ትውልዶች አሕዛብን ሁሉ በገዛ ራሳቸው ጐዳና ይሄዱ ዘንድ ተዋቸው። 17ከዚህም ሁሉ ጋር መልካም ሥራ እየሠራ፥ ከሰማይ ዝናብን ፍሬ የሚሆንበትንም ወራት ሲሰጠን፥ ልባችንንም በመብልና በደስታ ሲሞላው ራሱን ያለ ምስክር አልተወም። 18ይህንም ብለው እንዳይሠዉላቸው ሕዝቡን በጭንቅ አስተዉአቸው።

19አይሁድ ግን ከአንጾኪያና ከኢቆንዮን መጡ፤ ሕዝቡንም አባብለው ጳውሎስን ወገሩ የሞተም መስሎአቸው ከከተማ ወደ ውጭ ጐተቱት። 20ደቀ መዛሙርት ግን ከበውት ሳሉ፥ ተነስቶ ወደ ከተማ ገባ። በነገውም ከበርናባስ ጋር ወደ ደርቤን ወጣ።

21በዚያችም ከተማ ወንጌልን ሰብከው እጅግ ደቀ መዛሙርትን ካደረጉ በኋላ፥ የደቀ መዛሙርትን ልብ እያጸኑ በሃይማኖትም ጸንተው እንዲኖሩ እየመከሩና። ወደ እግዚአብሔር መንግሥት በብዙ መከራ እንገባ ዘንድ ያስፈልገናል እያሉ፥ ወደ ልስጥራን ወደ ኢቆንዮንም ወደ አንጾኪያም ተመለሱ። 22 23በየቤተ ክርስቲያኑም ሽማግሌዎችን ከሾሙላቸው በኋላ ጦመውም ከጸለዩ በኋላ፥ ላመኑበት ለጌታ አደራ ሰጡአቸው።

24በጲስድያም አልፈው ወደ ጵንፍልያ መጡ፥ 25በጴርጌንም ቃሉን ከተናገሩ በኋላ ወደ አጣልያ ወረዱ፥

26ከዚያም ስለ ፈጸሙት ሥራ ለእግዚአብሔር ጸጋ አደራ ወደ ተሰጡበት ወደ አንጾኪያ በመርከብ ሄዱ። 27በደረሱም ጊዜ ቤተ ክርስቲያኑን ሰብስበው እግዚአብሔር ከእነርሱ ጋር ያደረገውን ሁሉ ለአሕዛብም የሃይማኖትን ደጅ እንደ ከፈተላቸው ተናገሩ። 28ከደቀ መዛሙርትም ጋር አያሌ ቀን ተቀመጡ።

Revised Amharic Bible in XML (2003). Printed version by United Bible Societies (C)1962. E-Text in transliterated ASCII format by Lapsley/Brooks Foundation 1994. Unicode UTF-8 transformation and XML-tagging by Dirk Röckmann 2003 (www.nt-text.net). -- With kind permission of the Bible Society of Ethiopia. Every non-commercial work using this data in any form must fully include this copyright statement! Every commercial use of parts or the complete data in any form needs written permission of the Bible Society of Ethiopia!

Bible Hub

Acts 13
Top of Page
Top of Page