2ኛ ወደ ጢሞቴዎስ 4
Amharic NT

1በእግዚአብሔር ፊት በሕያዋንና በሙታንም ሊፈርድ ባለው በጌታ በኢየሱስ ክርስቶስ ፊት፥ በመገለጡና በመንግሥቱም እመክርሃለሁ፤ 2ቃሉን ስበክ፥ በጊዜውም አለጊዜውም ጽና፥ ፈጽመህ እየታገሥህና እያስተማርህ፥ ዝለፍና ገሥጽ ምከርም። 3ሕይወት የሚገኝበትን ትምህርት የማይታገሡበት ዘመን ይመጣልና፤ ነገር ግን ጆሮቻቸውን የሚያሳክክ ስለ ሆነ፥ እንደ ገዛ ምኞታቸው ለራሳቸው አስተማሪዎችን ያከማቻሉ። 4እውነትንም ከመስማት ጆሮቻቸውን ይመልሳሉ፥ ወደ ተረትም ፈቀቅ ይላሉ። 5አንተ ግን ነገርን ሁሉ በልክ አድርግ፥ መከራን ተቀበል፥ የወንጌል ሰባኪነትን ሥራ አድርግ፥ አገልግሎትህን ፈጽም።

6በመሥዋዕት እንደሚደረግ፥ የእኔ ሕይወት ይሠዋልና፥ የምሄድበትም ጊዜ ደርሶአል። 7መልካሙን ገድል ተጋድዬአለሁ፥ ሩጫውን ጨርሼአለሁ፥ ሃይማኖትን ጠብቄአለሁ፤ 8ወደ ፊት የጽድቅ አክሊል ተዘጋጅቶልኛል፥ ይህንም ጻድቅ ፈራጅ የሆነው ጌታ ያን ቀን ለእኔ ያስረክባል፥ ደግሞም መገለጡን ለሚወዱት ሁሉ እንጂ ለእኔ ብቻ አይደለም።

9በቶሎ ወደ እኔ እንድትመጣ ትጋ፤ 10ዴማስ የአሁኑን ዓለም ወዶ ትቶኛልና፥ ወደ ተሰሎንቄም ሄዶአል፤ ቄርቂስም ወደ ገላትያ ቲቶም ወደ ድልማጥያ ሄደዋል፤ 11ሉቃስ ብቻ ከእኔ ጋር አለ። ማርቆስ ለአገልግሎት ብዙ ይጠቅመኛልና ይዘኸው ከአንተ ጋር አምጣው። 12ቲኪቆስን ግን ወደ ኤፌሶን ላክሁት። 13ስትመጣ በጢሮአዳ ከአክርጳ ዘንድ የተውሁትን በርኖሱንና መጻሕፍቱን ይልቁንም በብራና የተጻፉትን አምጣልኝ። 14የናስ አንጥረኛው እስክንድሮስ እጅግ ከፋብኝ፤ ጌታ እንደ ሥራው ይመልስለታል። 15አንተም ደግሞ ከእርሱ ተጠበቅ፥ የምንናገረውን እጅግ ተቃውሞአልና።

16በፊተኛው ሙግቴ አንድ ስንኳ አልደረሰልኝም፥ ሁሉም ተዉኝ እንጂ፤ ይህንም አይቍጠርባቸው፤ 17ዳሩ ግን የስብከቱ ሥራ በእኔ እንዲፈጸም አሕዛብም ሁሉ እንዲሰሙት፥ ጌታ በእኔ አጠገብ ቆሞ አበረታኝ፥ ከአንበሳ አፍም ዳንሁ። 18ጌታም ከክፉ ነገር ሁሉ ያድነኛል ለሰማያዊውም መንግሥት ይጠብቀኛል፤ ለእርሱ ከዘላለም እስከ ዘላለም ክብር ይሁን፤ አሜን።

19ለጵርስቅላና ለአቂላ ለሄኔሲፎሩም ቤተ ሰዎች ሰላምታ አቅርብልኝ። 20ኤርስጦስ በቆሮንቶስ ቀረ፥ ጥሮፊሞስን ግን ታሞ በሚሊጢን ተውሁት። 21ከክረምት በፊት እንድትመጣ ትጋ። ኤውግሎስና ጱዴስ ሊኖስም ቅላውዲያም ወንድሞችም ሁሉ ሰላምታ ያቀርቡልሃል።

22ጌታ ኢየሱስ ክርስቶስ ከመንፈስህ ጋር ይሁን። ጸጋ ከእናንተ ጋር ይሁን፤ አሜን።

Revised Amharic Bible in XML (2003). Printed version by United Bible Societies (C)1962. E-Text in transliterated ASCII format by Lapsley/Brooks Foundation 1994. Unicode UTF-8 transformation and XML-tagging by Dirk Röckmann 2003 (www.nt-text.net). -- With kind permission of the Bible Society of Ethiopia. Every non-commercial work using this data in any form must fully include this copyright statement! Every commercial use of parts or the complete data in any form needs written permission of the Bible Society of Ethiopia!

Bible Hub

2 Timothy 3
Top of Page
Top of Page