2ኛ የጴጥሮስ መልእክት 2
Amharic NT

1ነገር ግን ሐሰተኞች ነቢያት ደግሞ በሕዝቡ መካከል ነበሩ እንዲሁም በመካከላችሁ ደግሞ ሐሰተኞች አስተማሪዎች ይሆናሉ፤ እነርሱም የዋጃቸውን ጌታ እንኳ ክደው የሚፈጥንን ጥፋት በራሳቸው ላይ እየሳቡ የሚያጠፋ ኑፋቄን አሹልከው ያገባሉ፤ 2ብዙዎችም በመዳራታቸው ይከተሉአቸዋል በእነርሱም ጠንቅ የእውነት መንገድ ይሰደባል። 3ገንዘብንም በመመኘት በተፈጠረ ነገር ይረቡባችኋል፤ ፍርዳቸውም ከጥንት ጀምሮ አይዘገይም ጥፋታቸውም አያንቀላፋም።

4እግዚአብሔር ኃጢአትን ላደረጉ መላእክት ሳይራራላቸው ወደ ገሃነም ጥሎ በጨለማ ጉድጓድ ለፍርድ ሊጠበቁ አሳልፎ ከሰጣቸው፥ 5ለቀደመውም ዓለም ሳይራራ ከሌሎች ሰባት ጋር ጽድቅን የሚሰብከውን ኖኅን አድኖ በኃጢአተኞች ዓለም ላይ የጥፋትን ውኃ ካወረደ፥ 6ኃጢአትንም ያደርጉ ዘንድ ላሉት ምሳሌ አድርጎ ከተማዎችን ሰዶምንና ገሞራን አመድ እስኪሆኑ ድረስ አቃጥሎና ገልብጦ ከፈረደባቸው፥

7ጻድቅ ሎጥም በመካከላቸው ሲኖር እያየና እየሰማ ዕለት ዕለት በዓመፀኛ ሥራቸው ጻድቅ ነፍሱን አስጨንቆ ነበርና በዓመፀኞች ሴሰኛ ኑሮ የተገፋውን ያን ጻድቅ ካዳነ፥ 8 9ጌታ እግዚአብሔርን የሚያመልኩትን ከፈተና እንዴት እንዲያድን፥ በደለኞችንም ይልቁንም በርኵስ ምኞት የሥጋን ፍትወት እየተከተሉ የሚመላለሱትን ጌትነትንም የሚንቁትን እየቀጣቸው ለፍርድ ቀን እንዴት እንዲጠብቅ ያውቃል። ደፋሮችና ኵሩዎች ሆነው ሥልጣን ያላቸውን ሲሳደቡ አይንቀጠቀጡም፤

10 11ዳሩ ግን መላእክት በኃይልና በብርታት ከእነርሱ ይልቅ ምንም ቢበልጡ በጌታ ፊት በእነርሱ ላይ የስድብን ፍርድ አያመጡም። 12እነዚህ ግን ለመጠመድና ለመጥፋት በፍጥረታቸው እንደ ተወለዱ አእምሮ እንደ ሌላቸው እንስሶች ሆነው፥ በማያውቁት ነገር እየተሳደቡ በጥፋታቸው ይጠፋሉ፤ 13የዓመፃቸውን ደመወዝ ይቀበላሉ። በቀን ሲዘፍኑ እንደ ተድላ ይቆጥሩታል፤ ነውረኞችና ርኵሳን ሆነው ከእናንተ ጋር ሲጋበዙ በፍቅር ግብዣ ይዘፍናሉ፤ 14ምንዝር የሞላባቸው ኃጢአትንም የማይተዉ ዓይኖች አሉአቸው፤ የማይጸኑትን ነፍሳት ያታልላሉ፤ መመኘትን የለመደ ልብ አላቸው፤ የተረገሙ ናቸው። 15ቅንን መንገድ ትተው ተሳሳቱ፤ የባሶርን ልጅ የበለዓምን መንገድ ተከተሉ፤ እርሱ የዓመፃን ደመወዝ ወደደ፥ 16ነገር ግን ስለ መተላለፉ ተዘለፈ፤ ቃል የሌለው አህያ በሰው ቃል ተናግሮ የነቢዩን እብድነት አገደ።

17ድቅድቅ ጨለማ ለዘላለም የተጠበቀላቸው እነዚህ ውኃ የሌለባቸው ምንጮች በዐውሎ ነፋስም የተነዱ ደመናዎች ናቸው። 18ከንቱና ከመጠን ይልቅ ታላቅ የሆነውን ቃል ይናገራሉና፥ በስሕተትም ከሚኖሩት አሁን የሚያመልጡትን በሥጋ ሴሰኛ ምኞት ያታልላሉ። 19ራሳቸው የጥፋት ባሪያዎች ሆነው። አርነት ትወጣላችሁ እያሉ ተስፋ ይሰጡአቸዋል፤ ሰው ለተሸነፈበት ለእርሱ ተገዝቶ ባሪያ ነውና። 20በጌታችንና በመድኃኒታችን በኢየሱስ ክርስቶስ እውቀት ከዓለም ርኵሰት ካመለጡ በኋላ ዳግመኛ በእርስዋ ተጠላልፈው የተሸነፉ ቢሆኑ፥ ከፊተኛው ኑሮአቸው ይልቅ የኋለኛው የባሰ ሆኖባቸዋል። 21አውቀዋት ከተሰጣቸው ከቅድስት ትእዛዝ ከሚመለሱ የጽድቅን መንገድ ባላወቋት በተሻላቸው ነበርና። 22ውሻ ወደ ትፋቱ ይመለሳል፥ ደግሞ። የታጠበች እርያ በጭቃ ለመንከባለል ትመለሳለች እንደሚባል እውነተኞች ምሳሌዎች ሆኖባቸዋል።

Revised Amharic Bible in XML (2003). Printed version by United Bible Societies (C)1962. E-Text in transliterated ASCII format by Lapsley/Brooks Foundation 1994. Unicode UTF-8 transformation and XML-tagging by Dirk Röckmann 2003 (www.nt-text.net). -- With kind permission of the Bible Society of Ethiopia. Every non-commercial work using this data in any form must fully include this copyright statement! Every commercial use of parts or the complete data in any form needs written permission of the Bible Society of Ethiopia!

Bible Hub

2 Peter 1
Top of Page
Top of Page