2ኛ ወደ ቆሮንቶስ ሰዎች 7
Amharic NT

1እንግዲህ፥ ወዳጆች ሆይ፥ የዚህ ተስፋ ቃል ካለን፥ በእግዚአብሔር ፍርሃት ቅድስናን ፍጹም እያደረግን ሥጋንና መንፈስን ከሚያረክስ ሁሉ ራሳችንን እናንጻ።

2በልባችሁ ስፍራ አስፉልን፤ ማንንም አልበደልንም፥ ማንንም አላጠፋንም፥ ማንንም አላታለልንም። 3ለኵነኔ አልልም፤ በአንድነት ለመሞትና በአንድነት ለመኖር በልባችን እንዳላችሁ አስቀድሜ ብዬአለሁና። 4ስለ እናንተ እምነቴ ታላቅ ነው፥ በእናንተ ምክንያት ትምክህቴ ታላቅ ነው፤ መጽናናት ሞልቶብኛል፤ በመከራችን ሁሉ ደስታዬ ከመጠን ይልቅ ይበዛል።

5ወደ መቄዶንያም በመጣን ጊዜ፥ በሁሉ ነገር መከራን ተቀበልን እንጂ ሥጋችን ዕረፍት አልነበረውም፤ በውጭ ጠብ ነበረ፥ በውስጥ ፍርሃት ነበረ። 6ነገር ግን ኀዘንተኞችን የሚያጽናና አምላክ በቲቶ መምጣት አጽናናን፤ 7በመምጣቱም ብቻ አይደለም ነገር ግን ናፍቆታችሁንና ልቅሶአችሁን ስለ እኔም ቅንዓታችሁን ሲናገረን በእናንተ ላይ በተጽናናበት መጽናናት ደግሞ ነው፤ ስለዚህም ከፊት ይልቅ ደስ አለን። 8በመልእክቴ ያሳዘንኋችሁ ብሆን እንኳ አልጸጸትም፤ የተጸጸትሁ ብሆን እንኳ፥ ያ መልእክት ጥቂት ጊዜ ብቻ እንዳሳዘናችሁ አያለሁና አሁን ለንስሐ ስላዘናችሁ ደስ ብሎኛል እንጂ ስላዘናችሁ አይደለም፤ 9በምንም ከእኛ የተነሣ እንዳትጎዱ እንደ እግዚአብሔር ፈቃድ አዝናችኋልና። 10እንደ እግዚአብሔር ፈቃድ የሆነ ኀዘን ጸጸት የሌለበትን፥ ወደ መዳንም የሚያደርሰውን ንስሐ ያደርጋልና፤ የዓለም ኀዘን ግን ሞትን ያመጣል። 11እነሆ፥ ይህ እንደ እግዚአብሔር ፈቃድ የሆነ ኀዘን እንዴት ያለ ትጋት፥ እንዴት ያለ መልስ፥ እንዴት ያለ ቁጣ፥ እንዴት ያለ ፍርሃት፥ እንዴት ያለ ናፍቆት፥ እንዴት ያለ ቅንዓት፥ እንዴት ያለ በቀል በመካከላችሁ አደረገ። በዚህ ነገር ንጹሐን እንደ ሆናችሁ በሁሉ አስረድታችኋል። 12እንግዲያስ የጻፍሁላችሁ ብሆን እንኳ፥ ስለ እኛ ያላችሁ ትጋታችሁ ከእናንተ ዘንድ በእግዚአብሔር ፊት እንዲገለጥ እንጂ፥ ስለ በዳዩ ወይም ስለ ተበዳዩ አልጻፍሁም። ስለዚህ ተጽናንተናል። 13በመጽናናታችንም ስለ ቲቶ ደስታ አብልጦ ደስ አለን፥ መንፈሱ በሁላችሁ ዐርፎአልና፤ 14ለእርሱ በምንም ስለ እናንተ የተመካሁ እንደ ሆነ አላፈርሁምና፥ ነገር ግን ሁሉን ለእናንተ በእውነት እንደ ተናገርን፥ እንደዚህ ደግሞ ትምክህታችን በቲቶ ፊት እውነት ሆነ። 15ስለዚህም በፍርሃትና በመንቀጥቀጥ እንዴት እንደተቀበላችሁት፥ የሁላችሁን መታዘዝ እያሰበ ፍቅሩ በእናንተ ላይ እጅግ በዝቶአል። 16በነገር ሁሉ ተማምኜባችኋለሁና ደስ ይለኛል።

Revised Amharic Bible in XML (2003). Printed version by United Bible Societies (C)1962. E-Text in transliterated ASCII format by Lapsley/Brooks Foundation 1994. Unicode UTF-8 transformation and XML-tagging by Dirk Röckmann 2003 (www.nt-text.net). -- With kind permission of the Bible Society of Ethiopia. Every non-commercial work using this data in any form must fully include this copyright statement! Every commercial use of parts or the complete data in any form needs written permission of the Bible Society of Ethiopia!

Bible Hub

2 Corinthians 6
Top of Page
Top of Page