1ኛ ወደ ቆሮንቶስ ሰዎች 9
Amharic NT

1እኔ ነጻ አይደለሁምን? ሐዋርያስ አይደለሁምን? ጌታችንን ኢየሱስ ክርስቶስንስ አላየሁትምን? እናንተስ በጌታ ሥራዬ አይደላችሁምን? 2የሐዋርያነቴ ማኅተም በጌታ እናንተ ናችሁና ለሌሎች ሐዋርያ ባልሆን ለእናንተስ ምንም ቢሆን ሐዋርያ ነኝ።

3ለሚመረምሩኝ መልሴ ይህ ነው። ልንበላና ልንጠጣ መብት የለንምን? 4 5እንደ ሌሎቹ ሐዋርያትና እንደ ጌታ ወንድሞች እንደ ኬፋም፥ እኅት ሚስታችንን ይዘን ልንዞር መብት የለንምን? 6ወይስ ሥራን ለመተው መብት የሌለን እኔና በርናባስ ብቻ ነን? 7ከቶ በገዛ ገንዘቡ በወታደርነት የሚያገለግል ማን ነው? ወይስ ወይን ተክሎ ፍሬውን የማይበላ ማን ነው? ወይስ መንጋ እየጠበቀ ከመንጋው ወተት የማይጠጣ ማን ነው?

8ይህን በሰው ሥልጣን ብቻ እላለሁን? 9ሕግስ ደግሞ ያን አይልምን? የሚያበራየውን በሬ አፉን አትሰር ተብሎ በሙሴ ሕግ ተጽፎአልና። እግዚአብሔርስ ስለ በሬዎች ይገደዋልን? 10ይህን የሚለው ፈጽሞ ስለ እኛ አይደለምን? የሚያርስ በተስፋ ሊያርስ የሚያበራይም እንዲካፈል በተስፋ ሊያበራይ ስለሚገባው በእውነት ስለ እኛ ተጽፎአል። 11እኛ መንፈሳዊን ነገር የዘራንላችሁ ከሆንን የእናንተን የሥጋዊን ነገር እኛ ብናጭድ ትልቅ ነገር ነውን? 12ሌሎች በእናንተ ላይ ይህን መብት የሚካፈሉ ከሆኑ እኛማ ይልቁን እንዴታ? ነገር ግን የክርስቶስን ወንጌል እንዳንከለክል በሁሉ እንታገሣለን እንጂ በዚህ መብት አልተጠቀምንም። 13በመቅደስ ነገር የሚያገለግሉ ከመቅደስ የሆነውን ነገርን እንዲመገቡ፥ በመሠዊያውም የሚጸኑ ከመሠዊያው እንዲካፈሉ አታውቁምን? 14እንዲሁ ደግሞ ወንጌልን የሚሰብኩ ከወንጌል ቀለብ እንዲቀበሉ ጌታ ደንግጎአል።

15እኔ ግን ከእነዚህ ሁሉ ምንም አልተጠቀምሁም። እንዲህ እንዲሆንልኝ ይህን አልጽፍም፤ ማንም ትምክህቴን ከንቱ ከሚያደርግብኝ ሞት ይሻለኛልና። 16ወንጌልን ብሰብክ እንኳ የምመካበት የለኝም፤ ግድ ደርሶብኝ ነውና፤ ወንጌልንም ባልሰብክ ወዮልኝ። 17ይህን በፈቃዴ ባደርገው ደመወዝ አለኝና፤ ያለ ፈቃዴ ግን ባደርገው መጋቢነት በአደራ ተሰጥቶኛል። 18እንግዲህ ደመወዜ ምንድር ነው? ወንጌልን እየሰበክሁ በወንጌል ካለኝ መብት በሙሉ እንዳልጠቀም ወንጌልን ያለ ዋጋ ብናገር ነው።

19ከሰው ሁሉ አርነት የወጣሁ ስሆን የሚበልጡትን እንድጠቅም እንደ ባሪያ ራሴን ለሁሉ አስገዛለሁ። 20አይሁድንም እጠቅም ዘንድ ከአይሁድ ጋር እንደ አይሁዳዊ ሆንሁ፤ ከሕግ በታች ያሉትን እጠቅም ዘንድ፥ እኔ ራሴ ከሕግ በታች ሳልሆን፥ ከሕግ በታች ላሉት ከሕግ በታች እንዳለሁ ሆንሁ፤ 21ሕግ የሌላቸውን እጠቅም ዘንድ፥ ያለ እግዚአብሔር ህግ ሳልኖር ነገር ግን በክርስቶስ ሕግ በታች ሳለሁ፥ ሕግ ለሌላቸው ሕግ እንደ ሌለኝ ሆንሁ፤ 22ደካሞችን እጠቅም ዘንድ ለደካሞች እንደ ደካማ ሆንሁ፤ በሁሉ መንገድ አንዳንዶችን አድን ዘንድ፥ ከሁሉ ጋር በሁሉ ነገር እንደ እነርሱ ሆንሁ። 23በወንጌልም ማኅበረተኛ እሆን ዘንድ ስለ ወንጌል ሁሉን አደርጋለሁ።

24በእሽቅድምድም ስፍራ የሚሮጡት፥ ሁሉ እንዲሮጡ ነገር ግን አንዱ ብቻ ዋጋውን እንዲቀበል አታውቁምን? እንዲሁም ታገኙ ዘንድ ሩጡ። 25የሚታገልም ሁሉ በነገር ሁሉ ሰውነቱን ይገዛል፤ እነዚያም የሚጠፋውን አክሊል ሊያገኙ ነው፥ እኛ ግን የማይጠፋውን። 26ስለዚህ እኔ ያለ አሳብ እንደሚሮጥ ሁሉ እንዲሁ አልሮጥም፥ ነፋስን እንደሚጎስም ሁሉ እንዲሁ አልጋደልም፤ 27ነገር ግን ለሌሎች ከሰበክሁ በኋላ ራሴ የተጣልሁ እንዳልሆን ሥጋዬን እየጎሰምሁ አስገዛዋለሁ።

Revised Amharic Bible in XML (2003). Printed version by United Bible Societies (C)1962. E-Text in transliterated ASCII format by Lapsley/Brooks Foundation 1994. Unicode UTF-8 transformation and XML-tagging by Dirk Röckmann 2003 (www.nt-text.net). -- With kind permission of the Bible Society of Ethiopia. Every non-commercial work using this data in any form must fully include this copyright statement! Every commercial use of parts or the complete data in any form needs written permission of the Bible Society of Ethiopia!

Bible Hub

1 Corinthians 8
Top of Page
Top of Page